ራያ ዩኒቨርሲቲ የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ነው

116

ማይጨው መስከረም 18/2013( ኢዜአ) ራያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን ቅበላ አቅሙን ለማሳደግ የሚያግዘው የማስፋፊያ ግንባታ ከ333 ሚሊዮን ብር በሚልቅ ወጪ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

የማስፋፊያ  ግንባታው  በሰባት ህንጻዎች የተካተተ ነው።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋ ዓፈራ ለኢዜአ እንደተናገሩት የተቋሙ የማስፋፊያ  ግንባታ ሲጠናቀቅ  ከአራት ሺህ በላይ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።

ይህም አሁን ካሉት   3 ሺህ 300 ተማሪዎች በተጨማሪ ነው።

የተማሪዎች መኖሪያ ፣የመማሪያ ክፍሎች እና የመመገቢያ ዘመናዊ አዳራሽ በማስፋፊያ ህንጻዎች ውስጥ እየተካሄዱ ከሚገኙ ግንባታው ውስጥ  ተጠቅሰዋል።

የዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክት መሃንዲስ አቶ ፍሳሃ ደበሳይ በበኩላቸው፣ በሰባት ተቋራጮች እየተካሄደ ያለው ግንባታው በተያዘው ዓመት ባሉት አስር ወራት ውስጥ  እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ግንባታው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ዩኒቨርስቲው አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በግንባታው ሂደት እስካሁን ከ200 ለሚበልጡ ሰዎች   የስራ እድል እንዳገኙም ተመልክቷል።

ከተቋራጮቹ መካከል የአስገዶም አየለ ኮንስትራክሽን ግንባታ ተቋራጭ የፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሃፍቶም ገብረሚካኤል እንዳሉት፣  42 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ለማካሄድ በጨረታ አሸንፈው በገቡት ውል መሰረት የተረከቡት የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ከወር በፊት ጀምረዋል።

ራያ ዩኒቨርሲቲ  የመማር ማስተማር ስራው የጀመረው በ2010 ዓ.ም መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም