"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆን የልጅነት ህልሜ ነበር" አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

62

  አዲስ አበባ  መስከረም 18/2012 ( ኢዜአ) " የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆን የልጅነት ህልሜ ነበር " ሲል አዲስ የተሾመው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናገረ። ባልጠበቀው ጊዜ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ መመረጡንም ነው አሰልጣኝ ውበቱ የገለጸው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ መቀጠሩን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አሰልጣኝ ውበቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሥራውን ዛሬ የጀመረ ሲሆን በጋዜጠኞች ለተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

በአሰልጣኝነት የመቀጠርህን ሁኔታ እንዴት አገኘሀው? አሁን ውድድር በቆመበት ወቅት የብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኝነት መረከብህ ከባድ አይደለም ወይ? ተጫዋቾችን በምን አይነት መልኩ ነው የምትመርጠው? በቅጥር ሂደቱ ላይ ምን አስተያየት አለህ? የሚሉ ጥያቄዎች በዋነኛነት ለአሰልጣኙ ተነስተዋል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ "የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሆን ከልጅነቴ ጀምሮ አልመው የነበረ በመሆኑ ይህም ህልሜ በመሳካቱ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል" ብሏል።

"የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆንኩት ባልጠበቁት ጊዜ ነው፤ በዚህ ወቅት ስራውን አገኛለሁ ብሎ አላሰብኩም" ሲልም ገልጿል።

በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አማካኝነት ብሔራዊ ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ጥሩ መሻሻል በማሳየቱና አሰልጣኙ በዛው ይቀጥላል የሚል ግምት እንደነበረውም ተናግሯል።

በተጨማሪም ከሰበታ ከተማ ጋር የአንድ ዓመት ውል ይቀረው እንደነበረና ጥያቄው ሲቀርብለት ግን አገራዊ ኃላፊነት በመሆኑ የአሰልጣኝነቱን መንበር መረከቡን አመልክቷል።

ከዚህ በፊት ለአራትና አምስት ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ተወዳድሮ እንደሚያውቅና በአንድ አጋጣሚ አሰልጣኝ እንደሚሆን በይፋ ከተገለጸ በኋላ ውሳኔው መቀልበሱን አውስቷል።

ከዚህ በፊት የብሔራዊ ቡድንን እንዲያሰለጥን ለቀረበለት ጥያቄ አልቀበልም ብለህ ነበር ተብሎ ለተነሳለት አስተያየትም "እኔ የአሰልጥን ጥያቄ ቀርቦልኝ እምቢ አላልኩም" ሲል አሰልጣኝ ውበቱ ምላሽ ሰጥቷል።

"በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች ከስድስት ወር በላይ መቋረጣቸው በተጫዋቾች ብቃት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሆነና ብሔራዊ ቡድኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዘጋጀት ከባድ መሆኑን አያጠያየቅም" ብሏል።

በወረርሽኙ ምክንያት የእግር ኳስ ውድድሮች መቆማቸው ዓለም አቀፍ እውነታ እንደሆነና ተጫዋቾችን ወደ ቀደመ አቋማቸው ለመመለስ ጊዜ እንደሚወስደም ገልጿል።

አሁን ካለው አጭር ጊዜ አንጻር በቅድሚያ ተጨዋቾችን ሰፋ አድርጎ በመጥራት በቀጣይ እየታየ ለማጣሪያ ውድድሮች የሚያስፈልጉ ተጫዋቾች እንደሚመረጡ ነው አሰልጣኝ ውበቱ የጠቆመው።

ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ የሚደረግላቸው ነባርና አዲስ ተጫዋቾች ጥሪ ሊደረግላቸው እንደሚችልም አመልክቷል።

ተጫዋቾችን ወደ መስመር አስገብቶ ለጨዋታ ዝግጁ ማድረግ ከባድ ሥራ ቢሆንም የተቻለውን ጥረት ሁሉ እንደሚያደርግ አሰልጣኙ ገልጿል።

ካለው ጊዜ አንጻር በውጭ አገር ያሉ ተጫዋቾችን ትኩረቱን እንደማያደርግና በክለቦች ካለው ቆይታ አንጻር በአገር ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን የብሄራዊ ቡድኑ አባል ለማድረግ እንደማይቸገር ተናግሯል።

"አሰልጣኝ ሆኖ የሚቀጠር እሸንፋለሁ እንጂ ውጤት አላመጣም አይልም" ያለው አሰልጣኝ ውበቱ፣ በውሉ አማካኝነት የተቀመጡትን ግዴታዎች እንደተቀበለና የተጣለበትን ኃላፊነት ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርግ አመልክቷል።

የቅጥር ሂደቱን አስመልክቶ አሰልጣኝ ውበቱ በሰጠው አስተያያት በጉዳዩ ዙሪያ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽንን ማብራሪያ መጠየቁን ተናግሯል።

በእዚህም የቴክኒክ ኮሚቴው የማማከር ሚና እንዳለውና የመጨረሻ ውሳኔ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መሆኑንና ሂደቱም ህጋዊ አሰራር ስለመከተሉ ምላሽ እንደተሰጠው ገልጿል።

"ጉዳዩን አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርቤ አስተያየቴን ሰጥቻለሁ፤ በሂደቱ አካሄድ ላይ ጉድለቶች ቢኖሩ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነቱን አልቀበልም ነበር "ብሏል።  

በጋዜጣዊ መግለጫው ከጋዜጠኞች የተነሱ ሀሳቦች በአብዛኛው የግል አቋም የተንጸባረቀባቸው እንደሆነና አሁን የሚያስፈልገው ወደ ኋላ ማየትና መከፋፋል ሳይሆን ብሔራዊ ቡድኑን እንዴት እንገባው? የሚለው ጉዳይ እንደሆነ ነው አሰልጣኝ ውበቱ  በአጽንኦት የገለጸው።

አሰልጣኙ ከፌደሬሽኑ ጋር በተፈራረመው ውል መሰረት ሁለት ረዳት አሰልጣኝና አንድ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እንደሚመርጥ ቅጥሩም በእግር ኳስ ፌደሬሽን በኩል እንደሚፈጸም ተናግሯል።

ከቀድሞው አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳለውና አሰልጣኝ ሆኖ ከተሾመ በኋላም ከኢንስትራክተር አብርሃም የእንኳን ደስ አለህና የመልካም የሥራ ጊዜ ምኞት መግለጫ እንደደረሰው ተናግሯል።

"መቀጠር እንዳለ ሁሉ መባረርም አለ" ያለው አዲሱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ፣ "የመልቀቅና የመሰናበት ጉዳይ በውሉ በተቀመጡ ሁኔታዎች አማካኝነት ተፈጻሚ የሚሆን ጉዳይ ነው" ብሏል።

ከክለብ ይልቅ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆን የተሻለ የማሰቢያና የውሳኔ ጊዜ እንደሚሰጥ የገለጸው አሰልጣኝ ውበቱ፣ በቆይታው በብሔራዊ ቡድኑ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ እንደሚሰራ ገልጿል።

በካሜሮን ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች በህዳር ወር 2013 ዓ.ም መካሄድ የሚጀምሩ ሲሆን  በኳታር ለሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በሚካሄደው የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ውድድር በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ይጀምራል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን በህዳር ወር 2013 ዓ.ም ከኒጀር አቻው ጋር ያደርጋል።

ዋልያዎቹ በማጣሪያው በሚገኝበት ምድብ 11 የኮትዲቭዋር አቻውን አሸንፎ በማዳጋስካር ተሸንፎ በሦስት ነጥብ ከማዳጋስካር በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በኳታር የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ ስድስት ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ዚምባቤዌ ጋር የተደለደለ ሲሆን በቀጣይ ጊዜ በሚገለጽ መርሃ ግብር ጨዋታዎቹን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም