የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ ማኅበር ተመሠረተ

87

አዲስ አበባ መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) - የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ ማኅበር በይፋ ተመሠረተ።

ማኅበሩ በይፋ መመሥረቱን ተከትሎ በቀጣይ ሊሠራቸው ያሰባቸው ተግባራትን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ማኅበሩ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተመዝግቦ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሕጋዊ ሰውነት እንደተሰጠው ገልጿል።

ማኅበሩ የማስታወቂያ ሥራዎችን በመከታተል ብሎም በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ እንዲጎለብትና ወደ ኢንዱስትሪነት እንዲያድግ ለማስቻል ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አለባቸው ወዳይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በማስታወቂያ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን አጥንቶ በማውጣት እንዲፈቱ ማድረግ የማኅበሩ ቀዳሚ ተግባር ነው።

"የማስታወቂያ ድርጅቶችን በማቀፍ የተቋቋመው ይህ ማኅበር፣ ከዚህ ቀደም ችግሮችን በተናጠል ለመፍታት ይደረግ የነበረው ጥረት እምብዛም ውጤታማ ባለመሆኑ መሰባሰብና መደራጀቱ የመደመጥ ሁኔታን ከፍ ለማድረግ ያስችላል" ብለዋል።

በቀጣይ ጥራት ያላቸው የማስታወቂያ ሥራዎች እንዲሰሩና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ጥቅም እንዲከበር ለማድረግ ማኅበሩ የራሱን ሚና እንደሚወጣ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአገሪቱን ባህልና እሴት የጠበቁ የማስታወቂያ ሥራዎች ለሕዝብ እንዲቀርቡ ከማድረግ እንዲሁም ከማስታወቂያ ፖሊሲ አንጻር ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራም አቶ አለባቸው ተናግረዋል።

"ማኅበሩ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለተቸገሩ ሰዎች በዘመን መለወጫ በዓል ከ250 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለበዓል የሚሆኑ ቁሶችን ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለግንዛቤ ማስጨበጫ የሚያገለግሉ የቢልቦርድ ማስታወቂያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በመስቀል አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም