የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቅጥር ህጋዊ አሰራርን የተከለ ነው

69

አዲስ አበባ መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) "የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቅጥር ህጋዊ የአሰራር ሂደትን ተከትሎ የተካሄደ ነው" ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

አሰልጣኝ ውበቱ ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታ እንደተጣለበትም ገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ መቀጠሩን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ላይ "የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቅጥር ሂደት ግልጽነት ይጎለዋል፣ ወገንተኝነት የታየበት ነው የሚሉ ሀሳቦች በተለያዩ ወገኖች ይነሳሉ፤ በዚህ ላይ ማብራሪያ ቢሰጥበት" የሚል ጥያቄ በጋዜጠኞች ተነስቷል።

"የአሰልጣኙ ቅጥር የቴክኒክ ኮሚቴ ምክረ ሀሳቦችን መሰረት ያደረገ አይደለም። ይህም ጥያቄ ያስነሳል፤ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ማስቀጠል ለምን አልተፈለገም?" የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።

በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ "የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቅጥር ህጋዊ የአሰራር ሂደት ተከትሎ የተካሄደ ነው" ብለዋል።

ከዚህ በፊት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የተፈራረሙት የሁለት ዓመት ውል ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች በመራዘማቸው ምክንያት አሰልጣኙን ማቆየቱ አስፈላጊ ባለመሆኑ ከቡድኑ ጋር መለያየታቸውን አስታውሰዋል።

ኢንስትራክተር አብርሃም በተሰናበቱ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የውድድር መርሃ ግብር ማውጣቱን አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝን አስመልክቶ ምክረ ሀሳቦችን ለፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲያቀርብ መወሰኑን ነው አቶ ኢሳያስ ያስረዱት።

የቴክኒክ ኮሚቴው በአሰልጣኝ ቅጥር ላይ በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ አንድ ሰው ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ የተለያዩ አማራጮችን እንዲያቀርብ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ መጠየቁን ገልጸዋል።

ይሁንና የቴክኒክ ኮሚቴው ትኩረቱ አንድ ሰው መሆኑንና ይሾሙ በተባሉት አሰልጣኝ ያቀረባቸው ምክረ ሀሳቦችም በአብዛኛው አስተዳደራዊ እንጂ ቴክኒካዊ ጉዳዮች እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተጨማሪ ጊዜና አማራጮችን እንዲያቀርቡ ቢጠይቅም የቴክኒክ ኮሚቴው በአቋሙ መጽናቱን አመልክተዋል።

በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንዲቀጠሩ መወሰኑን ጠቁመዋል።

በፌዴሬሽኑ የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት ፌዴሬሽኑ በስሩ የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች እንደሚያቋቁም በግልጽ እንደሚያስቀምጥና የቴክኒክ ኮሚቴው በዚሁ አሰራር መቋቋሙን ገልጸዋል።

"በደንቡ መሰረት የቴክኒክ ኮሚቴ ምክረ ሀሳቦችን የማቅረብ እንጂ የመወሰን ስልጣን የለውም" ያሉት አቶ ኢሳያስ ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የቀረበለትን ምክረ ሀሳብ አለመቀበሉን ገልጸዋል።

በደንቡ ላይ ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝነት ቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ መቅጠር አለበት የሚል ነገር እንደሌለና ካለው አጭር ጊዜ አንጻር ኮሚቴው ተወያይቶ ያመነበትን ውሳኔ ማሳለፉን ነው ፕሬዚዳንቱ ያብራሩት።

በአጠቃላይ የአሰልጣኝ ቅጥሩ ሂደት ህጋዊ አሰራርን የተከተለና ህግን ያከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን የሁለት ዓመት ውል መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

ውላቸው ከመስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይም ገልጸዋል።

ጥቅማ ጥቅምን ሳይጨመር አሰልጣኝ ውበቱ ያልተጣራ 212 ሺህ ብር፤ የተጣራ 125 ሺህ ብር ወርሃዊ ክፍያ እንደሚያገኝም ጠቁመዋል።

አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን በካሜሮን ለሚካሄደው 33 ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍና በኳታር ለሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በሚካሄደው የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ውድድር ለመጨረሻው ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ የማድረስ ግዴታ እንዳለበት በውሉ ላይ መቀመጡንም ነው አቶ ባህሩ ያስረዱት።

"አሰልጣኙ በውሉ የተቀመጠውን ግዴታ ካላሟላ ይሰናበታል ማለት አይደለም" ብለዋል።

አሰልጣኙ ከብሔራዊ ቡድን መልቀቅ ከፈለገና ፌዴሬሽኑም አሰልጣኙን ማሰናበት ከፈለገ ይሄን ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች በውሉ ላይ በዝርዝር መቀመጣቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም