በመስቀልና በደመራ በዓል ላይ የታየው አብሮነት፣ አንድነትና ፍቅር በእሬቻ በዓልም ሊደገም ይገባል---ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

68

አዲስ አበባ፣መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) በመስቀልና በደመራ በዓል ላይ የታየው አብሮነት፣ አንድነትና ፍቅር በእሬቻ በዓልም ሊደገም ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባዋ የመስቀልና የደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማዋ ነዋሪዎችና የጸጥታ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረውን የሆራ ፊንፊኔ እሬቻ በዓል አከባበር አስመልክተው ምክትል ከንቲባዋ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዓሉ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ጠቁመው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መከላከልን መሰረት በማድረግ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንደሚከበርም አመልክተዋል።

በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች አባገዳዎች በሚያቀርቡት የመግቢያ ባጅ ብቻ በመጠቀም የሚታደሙ እንደሚሆንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

"የእሬቻ በዓል የሰላም እና የምስጋና በመሆኑ የተጣሉ የሚታረቁበትና ይቅር የሚባባሉበት በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ከዚህ ብዙ ሊማር ይገባል" ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
   ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የመስቀልና የደመራ በዓል አከባበር በሰላም በመጠናቀቁ ወይዘሮ አዳነች ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ለጸጥታ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዓሉ የሃይማኖት አባቶች ያስቀመጡትን መመሪያ በመከተልና እና ኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ አንድነትና አብሮነትን በማንጸባረቅ በሰላም መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡

የክረምት ወራት አልፎ ጸደይ ሲመጣ የሚከበረው አንደኛው በዓል "እሬቻ ብራ" የሚባል ሲሆን በውሃማ ሥፍራዎች የሚከበረው ነው።

ሌላኛው በበልግ ወቅት የሚከበረው "እሬቻ አርፋሳ" የተባለው በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በከፍታ ቦታዎች ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት እንደሆነ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም