በዞኑ በ20 ሺህ ሄክታር መሬት የጥጥ ልማት እየተካሄደ ነው

220

መተማ መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በዘንድሮ መኽር ወቅት 20 ሺህ ሄክታር መሬት የጥጥ ልማት እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌትነት በልሁ ለኢዜአ እንደገለፁት ጥራቱን የጠበቀ የጥጥ ምርት ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

የጥጥ ልማቱ በ8 ሺህ ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳና በ12 ሺህ ሄክታር የባለሀብቶች እርሻ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በጥጥ ልማቱ 2 ሺህ 600 አርሶ አደሮችና 300 ባለሃብቶች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"በመኽር ወቅቱ 600 ኩንታል የተላጨና በኬሚካል የታሸ የጥጥ ዘር ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል" ብለዋል ።

በአርሶ አደሮችና በባለሀብቶች እየለማ ካለው ጥጥ 400 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል ።

የጥጥ ምርቱ በዋናነት በገንዳ ውሃ ከተማ ለሚገኙ ሶስት የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች የሚቀርብ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል ።

በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ  ነዋሪ አርሶ አደር ደጀን ዋሴ በ20 ሄክታር መሬት ላይ የጥጥ ልማት እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

እያለሙ ካለው ጥጥ 400 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል፡፡

"አራት ሄክታር ማሳ ላይ እያለማሁ ካለሁት ጥጥ 80 ኩንታል ምርት እጠብቃለሁ" ያሉት ደግሞ በመተማ ወረዳ ቱመት መንዶካ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲሳይ ማሙየ ናቸው።

በገንዳ ውሃ ከተማ የአብድል ቃድር ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አብድልቃድር አህመድ በበኩላቸው ፋብሪካቸው በዓመት ከ90 ሺህ ኩንታል በላይ ጥጥ የመዳመጥ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

''አምራቾች የገበያ ችግር አይገጥማቸውም" ያሉት ባለሃብቱ ከ45 ባለሃብቶችና ከአስር አርሶ አደሮች  በወቅቱ በሚኖረው ዋጋ የጥጥ ምርት  ለመግዛት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው አመት በ16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከለማው ጥጥ 280 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም