በዞኑ 285 የዳስ መማሪያ ክፍሎች በህንጻ ግንባታ ተለወጡ

73

ሰቆጣ /ወልድያ መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን 285 የዳስ መማሪያ ክፍሎች ወደ ህንጻ ግንባታ መለወጣቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

በሰሜን ወሎም ከ56 ሚሊዮን ብር ባላይ ወጭ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት መዘጋጀታቸው ተነግሯል ።


የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ የግንባታ መሃንዲስ አቶ አራጋው አዲሱ ለኢዜአ  እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት አመት የመማሪያ ክፍሎቹን ወደ ግንባታ ለመለወጥ 86 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል ።

ለግንባታው ወጭ የተደረገው ገንዘብ በመንግስት፣ በሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት ፣ በቢ አይ ካ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በአትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴና በህዝቡ ተሳትፎ የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል ።

ከክልሉ ትምህርት ቢሮና ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመማሪያ ክፍሎቹ የተማሪዎች መቀመጫና ሌሎች ቁሳቁሶች ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል ።

በመምሪያው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ተጠሪ አቶ ፋንታው ስዩም በበኩላቸው በብሄረሰብ አስተዳደሩ ከ882 በላይ የዳስ ጥላ መማሪያ ክፍሎች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት የዳስ መማሪያ ክፍሎቹን ወደ ግንባታ ለመለወጥ 42 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል ።

በተያዘው በጀት አመትም 44 የዳስ መማሪያ ክፍሎችን ወደ ግንባታ ለመቀየር ማቀዱን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን በ58 ነጥብ 6  ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 50 ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ የኋላሸት ልዑልሰገድ  እንደገለጹት ትምህርት ቤቶቹ ባሏቸው 156 የመማሪያ ክፍሎች 7ሺህ 800 ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።

ትምህርት ቤቶቹን ስራ ለማስጀመር በ2 ነጥብ 2  ሚሊዮን ብር አንድ ሺህ 178 የተማሪ መቀመጫ ወንበሮች ተሰርተው እየተሰራጩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በ826 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 378 ሺህ ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም