አገራዊ ለውጡ ለሶማሌ ክልል ቱሪዝም ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል --- አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

186

አዲስ አበባ መስከረመ 17/2013(ኢዜአ)“ አገራዊ ለውጥ ከመጣ ወዲህ በሶማሌ ክልል አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ለቱሪዝም ልማት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ተናገሩ።

የዓለም የቱሪዝም ቀን  ለ41ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ “ቱሪዝም ለገጠር ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉን አስመልክቶ አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት “በቀጣይ አሥር ዓመት ኢትዮጵያ ወደብልጽግና ማማ ለመውጣት ከለየቻቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው” ብለዋል።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማትን ጨምሮ ዘርፉ የሚፈልጋቸውን የተለያዩ ሥራዎች በትኩረት  እንደሚያከናውኑም አመልክተዋል።

የቱሪዝም ዋነኛ ጉዳይ መሰረተ ልማት መዘርጋትና ሰላም ማስፈን  መሆኑን  ጠቅሰው፣ ክልሉም ለእነዚህ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

አገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ በክልሉ ሰላም ለማስፈን የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም አቶ ሙስጠፌ ተናግረዋል።

“በክልሉ ሰላም መስፈኑም ለቱሪዝም ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል” ብለዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው በበኩላቸው ከተለመዱ የቱሪዝም መዳረሻዎችና መስህቦች በዘለለ ያልተዳሰሰውንና ያልተነካውን በጥናት በመለየት ለዜጎች ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ለአብነትም በሶማሌ ክልል የሚገኙ የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ መዳረሻዎችን ማልማት ከተቻለ ተወዳዳሪ የመስህብ ሥፍራዎች እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

የገጠር ቱሪዝምን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ አስገንዝበው፣ሚኒስቴሩም ከክልሎች ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ቱሪዝም በገቢ ስርጭት ፍትሃዊነት ያለው ዘርፍ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሒሩት፣ ለእዚህም በአገር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን ነው የገለጹት።

“ክልሎችም ያልታዩ ሀብቶችን በማየትና በማልማት ለህዝቡ ያልተቋረጠ የገቢ ምንጭ ማመቻቸት አለባቸው” ሲሉም ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይ የሶማሌ ክልልን የቱሪዝም ሀብትና አገራዊ የቱሪዝም ገጽታን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በጂግጂጋ ከተማ እየተከበረ ያለውን የዓለም የቱሪዝም ቀን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ ለሚገነባው የባህል ማዕከል በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታዋሳል።

በዋናነት በሲፖዚየምና የቱሪስት መደራሻ ስፍራዎችን በመጎብኘት እየተከበረ ባለው በእዚህ በዓል ላይ የተለያዩ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና ጥሪ የተደረገላቸው የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም