የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቱሪስቶች ጥቆማ የሚሰጡባቸው የነጻ ስልክ ጥሪ ማዕከላት ሊያቋቁም ነው--የክልሉ ባህልና ቱሪዘም ቢሮ

126

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ቱሪስቶች የጸጥታ ስጋት ቢያጋጥማቸው ጥቆማ የሚሰጡባቸው የነጻ ስልክ ጥሪ ማዕከላት ሊቋቋም መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዘም ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ አሁን ላይ የፀጥታ ችግር ለቱሪስቶች እንቅስቃሴ ስጋት እያሳደረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በአገሪቱ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማስፋት አስተማማኝ ሰላምና ቱሪስቶች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ደህንነታቸው የተጠበቀ ማድረግ ግድ ይላል።

ከዚህ አኳያ የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል።

በ2013 ዓ.ም በክልሉ በሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኚዎች የጸጥታ ስጋት ቢያጋጥማቸው የሚያሳውቁበት የነጻ ስልክ ጥሪ ማዕከላት ለሟቋቋም ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ማዕከሉን በወንጪ ሐይቅ የቱሪስ መዳረሻ ለመጀመር መታሰቡንና ወደ ሌሎች መዳረሻዎች የማስፋት ተግባር ይከናወናልም ብለዋል።

በክልሉ በቱሪዝም መዳረሻዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን አስመለክቶ መረጃ የሚሰጡ ክፍሎች የማቋቋም እቅድ እንዳለም ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ በውስን አካባቢዎች ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ከበደ በቀጣይ በቂ የአስጎብኚ ድርጅቶችና አማራጭ የቱሪዝም ምርቶች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የቱሪዝም ምርቶችን አማራጭ በማስፋት የቱሪዝም ፍሰቱን ለመጨመር ስራዎች እንደሚከናወኑም ነው የገለጹት።

በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለቱሪዝም የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ሟሟላት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ድጋፍ የማድረግ ተግባር የበጀት ዓመቱ ዋንኛ  ትኩረት መሆኑንም አንስተዋል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የቱሪዝምን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ዩኒቨርሲቲ ፖሊስ ለማቋቋም በሙከራ ደረጃ ስራ እንደሚጀምር ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሸን መግለጹ የሚታወስ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም