ጥላቻ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል-- ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አበቡነ አብርሃም

156

ባህርዳር መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) ጥላቻን በማስወገድ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ማበርከት አለበት ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አበቡነ አብርሃም አስታወቁ። 

የመስቀል ደመራ በዓል ትላንት በባህርዳር ዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህር ዳር ከተማ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት መስቀል ኃይላችን፣ ቤዛችንና መድሃኒታችን ነው።

''በመስቀሉ አርማነት ጥላቻን እናስወግዳለን፣ ሰላምን እናሰፍናለን'' ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም "ትዕግስትንም አንግበን ወደፊት እንገሰግሳለን ሲሉም" ተናግረዋል።

"መስቀል ለሰው ልጆች የድህነትና የምህረት ምልክት በመሆኑ ሁሉም ጠብቆና ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስረክብ ይገባል " ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሁሉም ሀይማኖቶችና ህዝቦች ተከባብረውና ተስማምተው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

መስቀልና ሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውን ሳይለቁ እንዲከበሩ የከተማ አስተዳደሩ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነትን መሰረት አድርገው እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች ገደብ ሊበጅላቸው እንደሚገባ አመላክተዋል።

"እኩይ ተልዕኮ ያላቸው አካላት ጥቃትን በመከላከልና የውስጥ አንድነታችንን በመጠበቅ የጀመርነው የብልፅግና ጉዞ ከዳር ልናደርስ ይገባል " ብለዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ የባህር ዳር ከተማ የሰላም ከተማ ሆና እንድትቀጥልና የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓሉ በደሴና ደብረብረሀን ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ ከተሞች  በድምቀት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም