ሕዝባዊ በዓላት ምን ጊዜም ሰላማዊነታቸው ሊጠበቅ ይገባል -- የበዓል ታዳሚዎች

81

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013 (ኢዜአ) ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላት ምን ጊዜም ቢሆን ሰላማዊነታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አስትያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደመራ በዓል ታዳሚዎች ተናገሩ።

የ2013 ዓ.ም ደመራ በዓል በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት እንደወትሮው ብዙ ሰው ሳይታደምበት በአዲስ አበባ ተከብሯል።

ከመስቀል ደመራ በዓል ታዳሚዎች መካከል አስትያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ እንደሚሉት በዓላት ሰላማዊ ሆነው የበአሉን ድባብ በማድመቅ መከበር አለባቸው።

በዓላቱ የሚከበሩት የራሳቸውን ዓላማና እሴት ተላብሰው በመሆኑ የፖለቲካና መሰል አጀንዳዎች ሊንጸባረቁ አይገባም ብለዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ሰለሞን ዘሪሁን እንዳለው አሁን አሁን የሰላም ጉዳይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

አዳንድ ቡድኖች በዓላትን ጨምሮ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ፓለቲካዊ ፍላጎታቸውን ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል።

ይህም የህዝቡን ሰላምና የበዓላቱንም መንፈስ የሚያውክ በመሆኑ ማቆሚያ ሊበጅለት ሁላችንም ልንከላከለው ይገባል ብሏል።

በስፍራው የደመራ በዓልን ሲያከብሩ ያገኘናቸው ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በበኩላቸው ክብረ በዓላት ከአገር ባለፈ የዓለም እየሆኑ በመምጣታቸው ሰለማዊነታቸው ሊጠበቅ ይገባል ብለዋል።

በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ለማስቻል ሁሉም ሰው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የበዓላቱን በጎ ነገሮች በማሳየት የተመዘገቡት በዓለም ቅርስነት እንዲዘልቁ ሌሎችም እንዲመዘገቡ የማድረግ ሃላፊነት የሁላችንም ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ቀሲስ ቴዎድሮስ ተክለጺዮንም ''አገር የምታድገው ሁሉም ለአገር መቆርቆር ሲችል ነው'' በማለት የዶክተር በለጠን ሃሳብ ይጋራሉ።

በቀጣይ መሰል በዓላት ሲከበሩ መንግስት የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶችን ማክብር እስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መምህር ዳኒኤል ሰይፈ ሚካኤልም ሰላም፣ ልማትና እድገትን የመሰሉ ነገሮች የሚመጡት በሁሉም ጥረት ሲታከልበት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ከነዚህ ነገሮች የሚጠቀመው ሁሉም እንደመሆኑ መጠን የጋራ ተሳትፎ ማድርግ ይገባልም ብለዋል።

በመሆኑም ''ሁላችንም የሚጠበቅብንን የመጨረሻ አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን'' ሲሉ መልእክታውን አስተላልፈዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ የሚከበር መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም