“መስቀል በዓል ስናነሳ አገልጋይነትን፣ የአባቶችን ታሪክ ማቆየትንና ህዝቡ ታታሪነትን ያስተምረናል” ምክትል ከንቲባ አዳነች

538

አዲስ አበባ  መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ  ከተማ ምክትል ከንቲባ   አዳነች አቤቤ ከበዓለ መስቀሉ አገልጋይነትን፣ የአባቶችን ታሪክ ጠብቆ ማቆየትን እና ህዝቡ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ታታሪነትን ልንማር ይገባል አሉ።

የደመራ በዓል   ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ሌሎች የዕምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ እየተከበረ ይገኛል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ህዝቡ ከበዓሉ ባህልን፣ ሀይማኖትንና ስነ-ምግባርን በአንድነት አስተሳስሮ ስለመያዝ ልንማር ይገባል ብለዋል።

ቅዱስ መስቀሉን ለመደበቅ ቆሻሻ ይጣልበት የነበረ ቢሆንም አርነት የሚያወጣ እውነትንና ተግባርን ቀብሮ ማስቀረት እንደማይቻልም ጭምር ያስተምረናል።

“እኛም ብዙ የመዲናችችንን ገጽታ የሚያቆሽሹ ጉዳዮች ቢኖሩብንም እውነትንና ታማኝነትን ይዘን በአብሮነትና በፍቅር ተያይዘን በመስራት ጥላቻን  አሽንፈን መውጣት አለብን” ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።

አዲስ አበባን የምንገነባው ከሚያራርቁን  አስተሳሰቦችና ተግባራትም ርቀን በአብሮነትና በአገልጋይነት መንፈስ ስንሰማራ ብቻ እንደሆነ ነው የመስቀሉ ታሪክ የሚያስገዝበው ብለዋል።

“ዛሬም ከፊታችን ተራራ ሆኖ ያስቸገረንን ድህነት በማሸነፍ ለብልጽግናችን ልንረባረብ ይገባል” ሲሉ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።

ወደ ብልጽግናው የምናደርገው ጉዞ አልጋ በአልጋ ባይሆንም እጅ ለእጅ ከተያያዝንና በአንድነት መንፈስ ከተጋገዝን የማንሻገረው ችግር የለም።   

“አንድ እንጨት ችቦ አይሰራም፤ አንድ ችቦም ደመራ አይሆንም” ያሉት ምክትል ከንተባዋ ደመራ ሆኖ ለማጉላትና መብራት ሆኖ ለማብራት ህብረት ያፈልገናል ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ኮሮናሻይረስን በመከላከልና ራሳችንን በመጠበቅ እንዲሁም ችግረኞችን በማሰብ እንዲያሳልፉ ምክትል ከንቲባዋ አሳስበዋል።

የደመራ በዓል ቅዱስ መስቀሉ በንግስት ዕሌኒ ከተቀበረበት በደመራው የዕጣን ጪስ ጠቋሚነት ከተደበቀበት ስፍራ ለማውጣት የደመራ ዕንጨቶች መስከረም 16 ቀን የሚደመሩበት የበዓለ መስቀሉ ዋዜማ ነው።

በዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዐበይት  በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡