መስቀል መድኀንና ሰላምን የሚሰጥ ነው ---ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ

106

መስከረም 16 2013 (ኢዜአ)  መስቀል መድኀንና  ሰላምን የሚሰጥ     አንድነትን የሚሰብክ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ፡፡

የ2013 መስቀል በዓል በመላው ኢትዮጵያ እየተከበረ ነው፡፡

ፓትርያርኩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣት በተገኙበት  የአዲስ አበባ  መስቀል አደባባይ   የመስቀል በአልን አስመልክተው  ባስተላለፉት  መልዕክት መስቀል  የሰላም የአንድነትና የድህነት መሰረት  መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የመስቀል ቤዛነት  አንዱ ለሌላው  የሚከፍለው  ዋጋ ነው ያሉት ፓትርያ ርኩ  ኢየሱስ ክርስቶስም በመስቀል ተሰቅሎ  ለሰው ልጆች ሁሉ የመስዋእትነትን  አብነት ያሳየበት ነውም  ብለዋል፡፡

 መስቀልን ባየን ቁጠር እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር  የምናስታውስበትና አዳኝነቱን፣ፍቅሩን፣ሰላሙንና አንድነትን የምናገኝበት  መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

  “እኛም የመስቀልን ትረጉም ካወቅን ሰላምን፣ አንድነትን እንገኛለን ወደ ሰላም ወደ ልማት  እንጂ ወደ ጥፋት አንዳናተኩር ያደርገናል” ብለዋል አቡነማትያስ፡፡

‹‹ዛሬ የምናየው ድርጊት ከመስቀል ተቃራኒ ነው መነቃቀፍ መጠላላቱን ያስተማረን ማን ይሆን›› በማለት ሲያጠይቁ ሰውን መጥላትና መለያየት የኢትዮጵያውያን ሃሳብ   አለመሆኑን  ተናግረዋል ፡፡

ኢትዮጵያዊያን አብሮ መብላትና መኖርን ለዘመናት አካብተው የያዙ ቅዱስ ህዝብ ናቸው  ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ “የኢትዮጵያን ባህል ጥለን በጽንፍ የቆምን ልሂቃን ነን፤ ሰፊው  ህዝብ ግን በሰላም በአንድነት መኖር የሚፈልግ ነው” ብለዋል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ልሂቃን በአንድነት ተመካክረው ችግሮችን እንዲፈቱ ጥሪ ሲያቀርቡ  ወጣቶችም ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ አለባችሁ ሲሉ አመልክተዋል፡፡

“መስቀል የጋራ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ቃል የምንገባበት ነው፡፡ አዲሱ ዓመትም የውይይት፤ የመስማማት እንዲሆን ሁላችንም መጣር አለብን” ያሉት አቡነ ማትያስ ምሁራን፤ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ተቋማት ልዩነትን ከሚያሰፉ ተግባራት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል ፡፡

በሃገራችን እየተከሰቱ የሚገኙ መሰናክሎችን ለማስተካከል ጥበብን፣ ማስተዋልንና ትዕግስትን  እንዲላበሱ  አባታዊ መልእክታቸውን   አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም