አለማችን ከገጠማት ቀውስ ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ መተባበር ነው

64

አዲስ አበባ  መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  አለማችን  ከገጠማት  ቀውስ   ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ መተባበር ነው ሲሉ ጠቅይ ሚኒስትር አብይ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት  በ75ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ  ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በ75ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ በአካባቢያዊና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በተደረገው የቪድዮ ኮንፍረንስ  ባደረጉት ንግግር

 በኮሮና ቫይረስ፣በህዳሴ ግድብ፣ በጎረቤት ሀገር የጸጥታ ጉዳዮች እንዲሁም  በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  ለአለማችን ትልቅ ስጋት ደቅኖባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በርካታ ዜጎችን ለማህበራዊ ቀውስ  መዳረጉን  ገልጸዋል።

አለም ከገጠማት አዙሪት ለመውጣት  ብቸኛ አማራጯ መተባበር ነውም ብለዋል።

ለዚህም ደግሞ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንና የበኩሏንም እየተወጣች እንደሆነች አስረድተዋል።

በሌላ በኩል  ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት የምትገነባው ታላቁ ህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ተጽዕኖ እንደማያደረስ አብራርተዋል።

ግድቡ የሚገነባውም የሃይል ፍላጎታችንን ለማሟላት መሆኑንም በማስረዳት ።

ያለዚህ ፕሮጀክት ከ65 ሚሊዮን በላይ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኘውን የኢትዮጵያን   ህዝብ የሃየል ፍላጎት ማሳካት እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።

 ኢትዮጵያ ፣ግብጽና ሱዳን በ2015 የተፈራረሙትን መርህ በማድረግ የሀገራቱን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እየገነባች  መሆኗን  ገልፀዋል፡፡

አለማችን እየገጠማት ካሉ ችግሮች መካከል አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ገልጸዋል።

ይህን በመገንዘብም ኢትዮጵያ የአርንጓዴ ልማት ስራ በማከናወን ላይ መሆኗን አብራርተዋል።

ጸጥታን በተመለከተም ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራት ሰላም እንዲጠበቅ የበኩሏን ድርሻ ተወጠታለች፣ እየተወጣችም ትገኛለች ብለዋል።

በሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደታ ላይ የተጫወተችውን ከፍተኛ ሚና  በምሳሌ በመጥቀስ ።

ከዚህ በተጨማሪም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አሸባሪ ቡድን አልሸባብ በመዋጋት በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ስራ እየሰራች ትገኛለች፡፡

በመጨረሻም የተመድ ተልዕኮውን ለማሳካት ለሚያደርገው ጥረት ኢትዮጵያ ከጎኑ እንደምትቆም  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም