የኦሮሚያ ባለሀብቶች ለወንጪ ኘሮጄክት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ

75

 አዲስ አበባ  መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) በገበታ ለሀገር ጥሪ መሰረት የኦሮሚያ ባለሀብቶች ለወንጪ ኘሮጄክት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በትናንትናው እለት 300 የሚሆኑ የኦሮሚያ ባለሀብቶች የተሳተፉበት ገበታ ለሀገር ገቢ የማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ተከናውኗል፡፡ባለሀብቶች ለክልሉ ብሎም ለሀገር ልማት እና እድገት ያደረጉት አስተዋጽኦ የሀገር ባለውለታነታቸውን የሚያሳይ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ባለሀብቶች በሄዱበት የመንግስት ተቋም ሁሉ በቀዳሚነት እንዲስተናገዱም አቶ ሽመልስ አብዲሳ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡በመርሀ ግብሩም ለወንጪ ኘሮጀክት በቢሊዮን ብሮች ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡት ባለሀብቶቹ በቀጣይም በሀገር የልማት ጥሪ ላይ ለመሳተፍም ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ወንጪ ሀይቅ ከአዲስ አበባ150 ኪ. ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ 3ሺ380 ሜትር ከፍታ ያለው በተራራ የተሸፈነ እና ብርቅዬ አእዋፍ፣ ፍል ውሃና ታሪካዊ ገዳማትን በውስጡ የያዘ የተፈጥሮ መስህብ ነው፡፡

እንደ ኢቢሲ ዘገባ ቦታው ሲለማም የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ በተሻለ ሁኔታ የሚያሰፋ ሲሆን፣ በስራ እድል ፈጠራና የተሻለ የቱርስት መስህብ እንዲሆን የሚያስችል ነው ፡፡


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም