ቻይና ለአፍሪካ አገራት አጋርነት የምትሰጠው ቦታ የላቀ ነው -የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ

64
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 ቻይና ለአፍሪካ አገራት አጋርነት የምትሰጠው ቦታ የላቀ ነው ሲሉ የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ሌ ዛን ሹን ተናገሩ። ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ሌ ዛን ሹን ዛሬ የአፍሪካ ህብረትን ጎብኝተዋል። እርሳቸውና የሚመሩት ቡድን የህብረቱ መቀመጫ የሆነውን ዘመናዊ ህንጻ ከጎበኘ በኋላ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ከአፍሪካ ህብረት የስራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል። አዲሱ የህብረቱ መቀመጫ ህንጻ በቻይናውያን መገንባቱ የሚታወስ ሲሆን አፈ-ጉባኤው ህንጻውን የቻይና-አፍሪካ ትብብርና አጋርነት ምርጥ ምልክት ነው ብለውታል። ህብረቱ አፍሪካዊያን በአንድነት ለመቆምና ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት ያቋቋሙት ነው ያሉት ሚስተር ሌ ለዚህም በቅርብ ጊዜ እየተተገበሩ የሚገኙት አጀንዳ 2063ና የልማትና የጋራ የአየር ቀጣና ፕሮጀክቶች የጥረቱ ምሳሌ ናቸው ብለዋል። አገራቸው አፍሪካዊያን ለመልማትና ከድህነት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትልቅ የልማት አጋር ሆና እየሰራች መሆኗን ጠቅሰዋል። የቻይና ህዝብም ለዘመናት አስከፊ ችግር ውስጥ የነበረ በመሆኑ “አገሬ ለአፍሪካ አገራት አጋርነት የምትሰጠው ቦታ የላቀ ነው” ብለዋል። በመሆኑም አገራቱ የህዝቦቻቸውን ህይወት ለመለወጥ የሚያደርጉትን ጥረት የመደገፉ ተግባር ወደፊትም ይቀጥላል፤ የቻይናና የአፍሪካ የልማት አጋርነትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። በሁለትዮሽ ምክክሩ ላይ የተገኙ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀ-መንበር ክዌዚ ኩዋርትይ በበኩላቸው ቻይና የአፍሪካ ልማት ልዩ አጋር ናት ሲሉ አሞካሽተዋል። ለዚህ ደግሞ ቻይና በአህጉሪቱ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ላይ የምታፈሰውን መዋዕለ-ነዋይ ለአብነት ጠቅሰዋል። ህብረቱ በተለያዩ የአህጉሪቱ ቀጣናዎች መካከል ለመፍጠር እየሞከረ ላለው ትስስርም ቻይና እንደ ድልድይ እያገለገለች ነው ብለዋል። ከዚህም ሌላ አገሪቱ በአፍሪካ ኢቦላን የመሳሰሉ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ያደረገችውን ድጋፍም አንስተዋል። ቻይና ከአንድ አመት በፊት ከአህጉረ አፍሪካ ጋር ለሁለንተናዊ ትብብር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም