የመስቀል በዓልን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር የተላለፈ መልእክት

70

 አዲስ አበባ  መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) የተከበራችሁ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ እያልን በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የዕድገት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን፡፡

ሕዝብ በመሰባሰብ በጋራ ደምቆ የሚከበር፣ ማኅበራዊ ትሥሥሩና ግንኙነቶች የሚጠናከሩበት ታላቅ በዓል ከመሆኑም በተጨማሪ በዓለም አቀፋዊ ቅርስነትም የተመዘገበ መሆኑ የበዓሉን ታላቅነት ያመላክታል፡፡

ይህን በየዓመቱ ደምቆ የሚከበረው በዓል ዘንድሮ በዓለም አቀፍና በሀገራችንም እየተሠራጨ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ መልኩ በቀነሰ መልኩ እንዲከበር አድርጎታል፡፡

አሁንም ይህ በሽታ ስርጭቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለመረጃ ያህልም እስካሁን በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 241 ሺህ 872 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው 72 ሺህ 173 ሰዎች የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን 273 ጽኑ ሕመም ላይ ናቸዉ፤ 1 ሺህ 155 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉም ተረጋግጧል፡፡

ለዚህ በሽታ መስፋፋት ደግሞ በዋነኛነት ኅብረተሰባችን በባለሙያዎች የሚሰጡትን የመከላከል እርምጃዎች በቸልተኝነትና በመዘናጋት በአግባቡ አለመፈፀሙ ነው፡፡

የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ቁጥር በሚደረጉ መሰባሰቦች የመሠራጨት ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ወቅት በአደባባይም ሆነ በሰፈር የሚከበረው የደመራ በዓል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ከመከላከል ትኩረት ጋር እንዲፈፀም የጤና ሚኒስቴር አበክሮ ያሳስባል፡፡

በበዓሉ ላይ የሚገኙ ሰዎች በተቻለ መጠን ርቀታቸውን በመጠበቅ ከመነካካት በመቆጠብ ደጋግመው በሳኒታይዘር እጃቸውን በማጽዳትና በምንም ዓይነት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብላቸውን ሳያወልቁ በዓሉን በሰላም አክብረው በሰላም ወደየቤታቸው እንዲመለሱ እንጠይቃለን፡፡

በጤንነትና በሕይወት ካለን በየዓመቱ ብዙ በዓሎችን እናከብራለን በሚል መርህ ኅብረተሰቡ እንዲንቀሳቀስ እያስታወስን በዓሉ የደስታ፣ የሰላምና የጤና እንዲሆን እንመኛለን፡፡

ጤና ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም