ዓመታዊው የዓለም የቱሪዝም ቀን ነገ ጂግጂጋ ላይ ይከበራል

113

አዲስ አበባ መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ ''ቱሪዝም ለገጠር ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ነገ በጂግጂጋ ከተማ ይከበራል።

መሪ ሀሳቡ ቱሪዝም የሚያስገኘው በረከት በከተሞች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በገጠር ለሚኖረውም ሕዝብ የዕድገት ምንጭ መሆን እንዳለበት የሚያመላክት ነው ተብሏል።

የዓለም ቱሪስቶች ትኩረት ንጹህ አየርና ጸጥታ የሠፈነበት የገጠር አካባቢ እየሆነ በመምጣቱ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም ተመላክቷል።

የዘንድሮው የቱሪዝም ቀን የሚከበርበት የሶማሌ ክልል እምቅ የቱሪዝም ሀብቱን ከተጠቀመበት ለቀጣይ የዕድገት ጉዞው የጎላ ሚና እንዳለውም ተጠቁሟል።

ክልሉ የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያን ጨምሮ የበርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።

የዓለም ቱሪዝም ቀን በጂግጂጋ ከተማ ሲከበር ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን ከተማዋ በ2008 ዓ.ም 28ኛውን የዓለም ቱሪዝም ቀንም ማስተናገዷን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ41ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም