በምሥራቅ ወለጋ ወጣቶች ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የድጋፍና ልማት ስራዎች አከናወኑ

58

ነቀምቴ መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን በክረምቱ የዜግነት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የድጋፍና ልማት ስራዎች ማከናወናቸውን የዞኑ የሴቶች፣ ሕፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ስራዎቹን ያከናወኑ በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች  የተሰማሩ በቁጥር ከ224ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ናቸው።

በጽህፈት ቤቱ  የወጣቶች የኢኮኖሚ ዕድገት እና እንቅስቃሴ አደረጃጀት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌቱ ቀነዓ ለኢዜአ እንደተናገሩት ወጣቶቹ  ባከናወኑት የድጋፍና ልማት ስራዎች ከ315ሺህ የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከስራዎቹም መካከል   514 ዩኒት ደም ልገሳ፣  112 የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ግንባታና ጥገና እንዲሁም 76 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ  ይገኙበታል።

በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ 2ሺህ 431 ወገኖች  ወጣቶቹ ከበጎ አድራጊዎች ያሰባሰቡትን  የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት እንዲሁም ለ2ሺህ 431 ችግረኛ ሕፃናት የጽህፈት መሣሪያዎችንና አልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስተባባሪው አብራርተዋል።

በዞኑ  የስሬ ከተማ ቀበሌ ሁለት ነዋሪ አቶ ተሾመ በንቲ በሰጡት አስተያየት ወድቆ የነበረ  ቤታቸው በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመጠገኑ ችግራቸው መቃለሉን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ  ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ደጊቱ ቴሶ በበኩላቸው ረዳት እንደሌላቸውና በእድሜ መግፋት ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተው  የአካባቢው ወጣቶች ባደረጉላቸው የምግብ ዘይትና ዱቄት ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

በበጎ አድራጎት ስራ ተሰማርተው ከነበሩ መካከል ወጣት ደገፈ ጌታቸው  በተለይም በደም እጦት የእናቶች ህይወት እንዳያልፍ ለመርዳት ለሶስተኛ ጊዜ  ደም መለገሱን ገልጾ በዚህም የመንፈስ እርካታ እንደሚሰማው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም