በመተማ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ 77 ሰዎች ተያዙ

109

መተማ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ 77 ሴቶችና ህፃናት መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ጫኔ እንደገለጹት  ህገ-ወጥ ተዘዋዋሪዎቹ ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ በተለያየ ጊዜና ቦታ ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ ናቸው።

ከመካከላቸውም 25 የሚሆኑት 18 ዓመት ያልሞላቸው ህፃናት ሲሆኑ መነሻቸው ከደቡብ ክልል እንደሆነ ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ህገ-ወጥ መካከል 37 የሚሆኑት ሱዳን ውስጥ ከገቡ በኋላ ከገዳሪፍ ግዛት በሱዳን የፀጥታ አካላት ተይዘው የተመለሱ መሆኑን ጠቁመው  ቀሪዎቹ ደግሞ በመተማ ወረዳ በተለያዩ ጫካ ውስጥ የተገኙ መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡

ሌሎች ለጊዜው ያልተገኙ ህገ-ወጥ ተዘዋዋሪዎች መኖራቸውንም ከጓደኞቻቸው ለመረዳት መቻሉን አስታውቀዋል።

''ከሱዳን ተይዘው ከተመለሱት መካከል የተደፈሩና አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች አሉ'' ያሉት ኃላፊዋ ለተጎጂዎች የምክርና የህክምና አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከተዘወዋሪዎች መካከል የ16 ዓመት ታዳጊና የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነቸው ማርታ ሲሳይ በሰጠችው አስተያየተ ከሁለት ሳምንት  በፊት ከሌሎች አምስት ጓደኞቿ ጋር በመሆን ጉዞ መጀመሯን ገልፃለች።

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን በመሄድ ገዳሪፍ ከደረሱ በኋላም ተይዘው መመለሳቸውን ተናግራለች።

''እኔ እድለኛ ሆኘ ተመልሻለሁ ከእኔ ጋር የነበሩት አምስት ጓደኞቼ ግን የት እንደገቡ አላውቅም'' ያለቸው ታዳጊዋ ሱዳን ከገቡ በኋላ በመንገድ ላይ ችግር እንደገጠማቸው አስረድታለች።

ለደላላ እያንዳንዳቸው 25 ሺህ ብር መክፈላቸውን ጠቅሳ፤በሰላም ወደ ወላጆቿ እጅ ከደረሰች ለሌሎች እኩዮቿ የደረሰባትን ስቃይና መከራ በማጋራት ህገ-ወጥ ስደትን እንዳያስቡ እንደምታስተምር ተናግራለች።

ሌላኛው  ነጻነት አበበ በበኩሏ ከአስር ቀናት በፊት ከዱራሜ ከተማ ተነስታ እንደመጣች ጠቅሳ  በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ለመግባት ሲሞክሩ ኬላው ላይ መያዛቸውን ተናግራለች፡፡

''ስንነሳ ሦስት ነበርን'' ያለችው ወጣቷ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ግን 18 መድረሳቸውን ገልጻለች፡፡

በዞኑ የማህበራዊ ልማት መምሪያ የስራ ስምሪት ቡድን መሪ አቶ ምርኩዝ ዘመነ በበኩላቸው ለህገ-ወጥ ተዘዋዋሪዎቹ የምግብና የመጠለያ አቅርቦት እየቀረበ ነው ብለዋል።

የትራንሰፖርት አቅርቦት በማመቻቸትም ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት  ብቻ በዞኑ መተማ በኩል ሊወጡ ሲሞክሩ የነበሩ  አንድ ሺህ 200 ወጣቶችና ህፃናት ተይዘው ወደ መጡበት አካባቢ መመለሳቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም