በጋሞና ወላይታ በተከሰተ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደረስ

68

አርባምንጭ/ሶዶ/ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ ) በጋሞና ወላይታ ዞኖች ሰሞኑን የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው የጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡

የጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ማርቆስ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ጎቆታ ወረዳ ኦታ ቀበሌ ከትናንት በስቲያ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት  ከአንድ ቤተሰብ የሶስት ሰዎች ህይወት አልፏል።

አደጋ የተከሰተው በዕለቱ  ሌሊት ሰባት ሰዓት አካባቢ መሆኑን አመልክተው 176 ሰዎች በመፈናቀላቸው  በአሁኑ ወቅት በቀበሌው በሚገኙ የመንግስት ተቋማት በጊዜያዊነት ተጠልለው እንድሚገኙ አስታውቀዋል።

ለተፈናቃዮቹ የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በወላይታ ዞን ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በተከታታይ የጣለው ከባድ ዝናብ በ12 ወረዳዎች ውስጥ  የጎርፍና  መሬት መንሸራተት አደጋ ማስከተሉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ ወልደማሪያም እንዳሉት በወረዳዎቹ በተከሰተው በዚሁ አደጋ ከሰባት ሺህ ሶስት መቶ በላይ ቤተሰቦች ተፈናቅለዋል፤ ከ500 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ጉዳት ደርሶበታል።

በአሁን ወቅት ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊ መጠለያ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ለተጎጂዎቹ  የሚውል  ከፌዴራልና ክልል የእህል ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

በዘላቂነት ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አማራጭ ስፍራ እየተዘጋጀ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

በዞኑ ጎርፍ ጉዳት ካደረሰባቸው የአበላ አባያ ወረዳ  አርሶ አደሮች መካከል የጨውከሬ ቀበሌ ነዋሪ  አቶ ሽመልስ ረታ በአደጋው ግምቱ ከአራት መቶ ሺህ ብር በላይ የሆነ የቀይ ሽንኩርት ማሳ እንደወደመባቸው ገልጸዋል፡፡


በመሬት የመንሸራተት ለሶስተኛ ጊዜ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳፈናቀላቸው የተናገሩት ደግሞ የካዎኮይሻ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ጎሰሞ ናቸው።

መንግስት በአፋጣኝ ተለዋጭ ቦታ  እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም