ለመስቀል በዓል በዶሮ እና በሽንኩርት ምርቶች ላይ መጠነኛ ቅናሽ ታይቷል

77

አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) ለመስቀል በዓል በዶሮና በሽንኩርት ምርቶች ላይ መጠነኛ ቅናሽ መታየቱን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ። በዓሉን ራስን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመጠበቅ ማክበር እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በሾላ ገበያ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገርቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች እንደተናገሩት በተለይ በዶሮና በሽንኩርት ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ  ታይቷል።

መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት በሸማቾች ማህበራት በኩል እየሰራ ያለውን የዋጋ ማረጋጊያ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ከሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ አካባቢ ዶሮ በማምጣት በሾላ ገበያ ሲነግዱ የነበሩት አቶ አየለ ተፈራ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት አንድ ዶሮ እንደክብደቱ ከ300 እስከ 500 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ካለፈው የፋሲካና የዘመን መለወጫ በዓላት ዋጋው ከ100 እስከ 150 ብር መቀነሱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት የመስቀል ገበያም መቀዛቀዙን አመልክተዋል፡፡

ከሰሜን ሸዋ ጂዳ ወረዳ ዶሮ ይዘው እንደመጡ የተናገሩት አቶ ገደፋ አቤቤ በበኩላቸው ዶሮዎቹን ከሰላሌ አካባቢ በውድ ዋጋ ገዝተው ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

አሁን እየሸጡበት ያለው የዶሮ ዋጋ ካለፉት ሁለት በዓላት ቅናሽ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ይህም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተጥሎ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜው ማለቁን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎትና ዋጋ ላይ ማሻሻያ በመደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሾላ ገበያ ዶሮ ሲገዙ የነበሩት ወይዘሮ ዓለም አለባቸው በበኩላቸው በተለያዩ ጊዚያት በምርት ላይ አንዴ ዋጋ ከተጨመረ ያማይወርድበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፣ አሁን ባለው ገበያ ግን የዶሮ ዋጋ የተሻለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መንግስት በየአካባቢው ያደራጃቸው የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማቅረብ ገበያውን በማረጋጋት በኩል ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት ነጋሽ የተባሉ ሌላው ሸማች በበኩላቸው የመስቀል በዓል ካለፉት በዓላት በዶሮና በሽንኩርት ምርቶች ላይ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ማህበረሰቡ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ትኩረት በመስጠትና ርቀቱን በመጠበቅ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ሌላዋ ሸማች ወይዘሮ አስናቁ አበራም "የዶሮ እና የሽንኩርት ገበያ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ነው" ብለዋል።

ባለፉት ሁለት በዓላት አንድ ኪሎ ሽንኩርት እስከ 35 ብር ሲገዙ እንደነበረና በአሁኑ ወቅት በሃያ ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት የመስቀል ደመራ በዓልን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከበሽታው በጠበቀ መልኩ እንደሚያከብሩ ገልጸው ሌሎችም በዚያ መልክ እንዲያከብሩ መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም