በኢንዱስትሪዎች ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

72

ሀዋሳ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የኢንዱስትሪ ሥራ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴር ዴኤታዋ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመገኘት ኮቪድ -19ኝን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን ጎብኝተዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንደገለጹት በርካታ ሀገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ኢንዱስትሪዎቻቸውን ቢዘጉም እርምጃው በኢኮኖሚያቸው ላይ ባሳደረው ጫና    የተነሳ መልሰው ለመክፈት ተገደዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ወረርሽኙ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ  ጉዳት እንዳያደርስ  የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች መውሰዱን  ጠቅሰዋል።

ኢንዱስትሪዎችን መዝጋት ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ችግሩን የከፋ ስለሚያደርገው አሰሪና ሰራተኞች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የምርት ሥራውም ሆነ የዜጎች እንቅስቃሴ ሳይገታ እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል።

የኢንዱስትሪዎች ሥራ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ  አሳስበዋል።

ለተግባራዊነቱም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ  አስገንዝበዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚይዙት ከፍተኛ የሰው ኃይል ቁጥር አንፃር ወረርሽኙን የመከላከል ሥራውን በከፍተኛ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አመላክተዋል ።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮሮናን በመከላከል የኢንዱስትሪ ሥራው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሙንጣሻ ብርሀኑ በበኩላቸው ኮቪድ-19ኝን ለመከላከላከል ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ጋር በቅርበት  ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከአሰሪና ሰራተኞቹ በተጨማሪ የከተማውን ነዋሪዎች ከቫይረሱ ለመጠበቅ የሚያግዙ  የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ በፓርኩ ውስጥ 22 የውጭና የሀገር ወስጥ ኩባንያዎች በምርት ሥራ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ኩባንያዎቹ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርኩ በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ ባለበት ወቅት ኮቬድ-19 መከሰቱንና ኢንዲስትሪዎች መዘጋት እንዳለባቸው ከየአቅጣጫው አስተያየቶች ሲሰጡ እንደነበርም አስታውሰዋል ።

"ይሁን እንጂ አስፈላጊው የሥራ ቦታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ የኢንዱስትሪ ሥራው እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል።

ከኮቪድ- 19 ጋር በተያያዘ  እስካሁን በፓርኩ ውስጥ አንድም የተዘጋ ኩባንያ አለመኖሩን ጠቁመዋል።

ፓርኩ በማህበረሰብ ሬዲዮና በተለያዩ ዘዴዎች ለሰራተኞቹ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ኩባንያዎችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማምረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙን የመከላከል ስራ እያገዙ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

በፓርኩ የኤቨረስት የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ሰራተኛ ወጣት ብዙነሽ ቡኤ ኮሮና በኢትዮጵያ በተከሰተበት ሰሞን ስጋት ውስጥ በመግባቷ ሥራዋን ለመቀጠል  ፈልጋ እንደነበር አስታውሳለች።

በፓርኩ ውስጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የምርት ሥራው መቀጠሉ ጊዜዋን በሥራ  እንድታሳልፍ እንደረዳት ገልጻለች ።

ለጥንቃቄ የሚሆኑ ቁሳቁሶችም እየቀረቡላቸው መሆኑን ተናግራላች።

በስነ ስርአቱ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የአሰሪና ሰራተኛ ኮንፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና የከተማ አስተዳደሩ አካላት ተገኝተዋል።

የችግኝ ተከላና ኮቪድ -19ኝን  ለመከላከል የሚረዳ መልዕክት ማስተላለፊያ ቢልቦርድም ተመርቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም