በሲዳማ ክልል ከ29 ሺህ ለሚበልጡ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው

54

ሀዋሳ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከ29 ሺህ ለሚበልጡ አባላቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገለፀ።
የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በሰጡት መግለጫ ለሶስት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና የፓርቲውን ዓላማና ግብ እንዲሁም  ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችና የመሻገሪያ ስልቶች ላይ ያተኮረ ነው።

በየደረጃው የሚገኙት የፖርቲው አባላት በስልጠናው ይህንን በመረዳት በውጤታማነት ተልኳቸው ለመፈጸም ያስችላቸዋል ብለዋል።

በተለይ ሃገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች በመረዳት በመደመር ዕሳቤ መምራትና ማገልገል የሚችሉት ውጤታማ ኃይል ለመፍጠር  እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

ቀደም ብሎ  በሁለት ዙር ከ4 ሺህ ለሚበልጡ ለፓርቲው ከፍተኛና  መካከለኛ አመራሮች መሰል ስልጠና መሰጠቱን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሀዋሳን ጨምሮ በ36 የወረዳና ክልል ማዕከላት በተዘጋጁ የስልጠና መድረኮች 29 ሺህ 382  አባላት እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካው ዘርፍ  ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመሻገር ባጠረ ጊዜ መካከለኛ ገቢ ያላት ሃገር  ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣትም ገንቢ ሚና እንደሚኖረው አቶ አብርሃም ተናግረዋል።

በተለይ የፓርቲው የፖለቲካ አቋምና ህብረ ብሄራዊነት ረገድ ተፈጥረው የነበሩ ብዥታዎች ከማጥራት አኳያ መግባባት ላይ ለመድረስና አንድ አቋም  ለመያዝ ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል።

አደናቃፊ ሃሳብና ተግባር የሚያራምዱ ልገምተኛ አመራሮች በማጣራት ወደመስመር የማስገባት እርምጃ ፓርቲው እየወሰደ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

በቀጣይ  በከተማና ገጠር ለሚገኙ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ስልጠናው እንደሚሰጥ አቶ አብርሃም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም