በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 20ሺህ ሜጋዋት ለማሳደግ ታቅዷል

39

አዳማ  መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ አሁን ያለውን ከ4ሺህ 500 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 20ሺህ ሜጋዋት ለማሳደግ መታቀዱን የውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና በተለይ  ለኢዜአ እንደተናገሩት  አሁን ያለው ኃይል የማመንጨት አቅም ከሀገሪቱ ልማትና እድገት ጋር የማይጣጣም ነው።

በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሴክተሮች፣ ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም ገልጸዋል።

እቅዱ እነዚህ መስኮች  የሚፈልጉትን ኃይል ከማቅረብ ባለፈ አሁን ያለውን 44 በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በቀጣይ አስር ዓመታት አሁን ያለውን ከ4ሺህ 500 ሜጋ ዋት የሀገሪቱን የኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 20ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ አቅደናል ብለዋል።

ይህም የኮይሻና የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ከንፋስ፣ ፀሐይ ኃይልና እንፋሎት አልምቶ በማመንጨት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህም ውስጥ በፀሐይ ኃይል ብቻ  165 ከተሞች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የገለጹት ዶክተር ፍሬህይወት ለገጠራማ አካባቢ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያገኙ አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሁን ያለውን 19ሺህ ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ በቀጣይ አስር ዓመታት ወደ 29ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በአቅርቦት ስርጭት ላይ  የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት የአገልግሎት ጥራት ከማሻሻል ባለፈ ያረጁ የስርጭት ኔትዎርኮችን  በአዳዲስ የመተካት ስራ ላይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በኢነርጂ ዘርፍ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የግሉ ሴክተር በስፋት በኃይል ማመንጫ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል ያሉት ደግሞ  የውሃ፣  መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር  ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ናቸው።

በተለይ በዘርፉ በመንግስት ከሚከናወነው ልማት ባሻገር በንፋስ፣ ፀሐይና እንፋሎት ኃይል የማመንጫ  ልማት ላይ  የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን  በስፋት  ለማሳተፍ መታቀዱንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከንፋስ፣ ፀሐይና እንፋሎት 820 ሜጋ ዋት ለማመንጨት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይነት በአእሻ፣ አሰላ፣ደብረብርሃንና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የኃይል ማመንጫ ግንባታ ይከናወናል ብለዋል።

በዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለሀገሪቱ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ከማዳረስ ባለፈ  የውጭ  ምንዛሪ ማስገኛ አንዱ ዘርፍ ለማድረግ  ጭምር  እንደሆነም አመልክተዋል።

በቀጣይ አስር  ዓመት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሴክተር ዕቅድ ዙሪያ  በአዳማ ከተማ የግምገማ መድረክ እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ መሆኑን ቀደም ሲል ዘግበናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም