የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገልን ድጋፍና ያሳየን አብሮነት ከደረሰብን ችግር ለመሻገር ድልድይ ሆኖናል - አቶ አወል አርባ

54

አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገልን ድጋፍና ያሳየን አብሮነት ከደረሰብን ችግር ለመሻገር ድልድይ ሆኖናል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ገለጹ።

የአፍሪካ ውሃ ድርጅት ባለቤት አቶ ሰኢድ ዳምጠው በበኩላቸው በአፋር ክልል በጎርፍ የተጎዱ ሰዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያልተቋረጠ  ድጋፍ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ውሃ ድርጅት በአፋር ክልል በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ግምቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሆነ የዱቄት ዘይትና አፍሪካ ውሃን ትናንት ድጋፍ አድርጓል።

የድርጅቱ ባለቤት አቶ ሰኢድ ዳምጠው ለተጎጂዎች የተሰጠውን ድጋፍ ሰመራ ከተማ በመገኘት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አወል አርባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ አፋር ክልል በኮቪድ-19፣ በአንበጣ መንጋ እና በጎርፍ አደጋ እየተፈተነ ነው።

በክልሉ አሚባራ እና አፋምቦ በሚባሉ ቦታዎች ላይ የአዋሽ ወንዝ አቅጣጫውን ስቶ በመውጣቱ የጎርፍ ውሃ በአርሶና አርብቶ አደሮች ላይ ጉዳት አድርሷል።

በአደጋው የሰው ሕይወት ባይጠፋም የቤት እንስሳትና ለመሰብሰብ የደረሱ የተለያዩ ሰብሎችን ጨምሮ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙ ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በክልሉ የደረሰው ጉዳት ከባድ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው ስለመሆኑ በተግባር ማየታቸውን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያዊያን ያደረጉልን ድጋፍና እያሳዩን ያለው አብሮነት ከደረሰብን ችግር ለመሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖናል" ብለዋል።

ችግሩ በክልሉ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ህብረተሰቡ ከጎናቸው በመሆን ላሳያቸው አብሮነትም ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል ምስጋና አቅርበዋል።

የአፍሪካ ውሃ አምራች ድርጅት ባለቤት አቶ ሰኢድ ዳምጠው "በአፋር ህዝብ ላይ የደረሰው ችግር በእኛ ላይ እንደደረሰ አድርገን ነው የምናየው" ብለዋል።

የተደረገው ድጋፍ የአፋር ህዝብን በጎርፍ አደጋ ከደረሰበት ችግር ሙሉ በሙሉ ማውጣት ባይችልም ከአፋር ህዝብ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ሲባል ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

" በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ የሚደርሰው ጉዳት የጋራ ጉዳታችን ነው " ያሉት አቶ ሰዒድ፣ ተጎጂዎች በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ ድረስ ድርጅቱ የጀመረውን ድጋፍ እንደማያቋርጥ አረጋግጠዋል።

በአፋር ህዝብ ላይ የደረሰውን ችግር በጋራ ለመፍታት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።  

በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ከ240 ሺህ በላይ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም 350 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ታውቋል።

የጎርፍ ተፈናቃዮች በአሁኑ ወቅት የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመድኃኒትና የመጠለያ ችግር እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ከ100 ሚሊዮን ብር አይበልጥም ተብሏል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም