የመገናኛ ብዙሃንና ማስታወቂያ ዘርፍ ራሱን በራሱ ለመምራት የሚስችለው መሪ እቅድ ተዘጋጀ

110

ቢሾፍቱ መስከረም 14/2013(ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃንና የማስታወቂያ ዘርፍ እራሱን በራሱ ለመምራት የሚያስቸለውን የአስር ዓመት መሪ እቅድ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ በመገናኛ ብዙሃንና ማስታወቂያ ዘርፍ የአስር ዓመት መሪ እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መክሯል።

በምክክር መድረኩ ዘርፉ በጥራትም ሆነ ተደራሽነት የሚፈለገው ያህል አለመስፋፋቱ፣ የህትመት ሚዲያውን አንቆ የያዘው ተግዳሮት አለመፈታቱ፣ በባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙሃን ሊደረጉ ከሚገባቸው ድጋፎች መካከል በስልጠና ብቻ ተገድቦ መቆየቱ ባለስልጣኑ ሊሻገራቸው ያልቻላቸው እንደሆኑ ተዳሰዋል።

ከዚህ ሌላ የብሮድካስት ፍላጎት መጨመር፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ጊዜውን መሰረት ያደረገ  ፖሊሲና ህጎች መውጣት፣  የመገናኛ ብዙሃንና የማስታወቂያ ካውንስሎች  መቋቋምና ወደ ስራ መግባት ደግሞ እቅዱን ለማዘጋጀት የተቃኙ ውስጣዊና ውጫዊ መልካም አጋጣሚዎች ሆነው በመነሻነት ቀርበዋል።

የብሮድካስት ባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ  ዘርፉ የሀገሪቷን ህዝብ ቁጥርና ብዝሃነትን የሚመጥን እንዲሁም ሁሉን አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ማጠናከርና ተደራሽነታቸውን ማስፋት የአስር  ዓመቱ መሪ እቅድ እንዲዘጋጅ መስገደዱን አብራርተዋል።

በባለስልጣኑ የዋና ዳይረክተሩ አማካሪና የእቅዱ አቅራቢ አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው መሪ እቅዱ የባለስልጣኑን የማስፈጸም አቅም ከማጎልበት ጎን ለጎን መገናኛ ብዙሃንም ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የሚፈቅድ መሆኑን ገልጸዋል።

እቅዱ በተለይም መገናኛ ብዙሃን የነበሩበትን ነባራዊ ሁኔታ አውቀው ለወደፊቱ ምንን ለማን ማሰራጨት እንደሚገባቸው የሚያመላክት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የውይይቱ ተሳታፊ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ አድማሱ ዳምጠው ናቸው።

ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳይና ዓለም አቀፋዊ የርዕዮተ ዓለም ሁኔታ በእቅዱ እንዴት እንደ ተቃኙ፣ የመገናኛ ብዙሃን መለያ መስፈርቶች ምን መሆን ይገባቸዋል የሚሉ ሐሳቦች ደግሞ በተሳታፊዎች ተነስተዋል።

በተጨማሪም  ሙያውና ፍላጎት ብቻ የተደበላለቀበት በመሆኑ ዘርፉ የማን ፣ መመራት የሚገባው በማን እና  የግብዓት እጥረት እንዴት እንደሚፈታ ፣ዘርፉን በቁጥር ብቻ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ መሬት ላይ የሚደረግ ድጋፍ ምን መምሰል አለባቸው  የሚሉ  ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ቀርበዋል።

በመሪ እቅዱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቱ ያስፈለገበት ምክንያት በራሱ አብሮ በምክክር እንዲሰራበትና የእቅዱ ግብዓት ሆኖ ምላሽ የሚያገኝበት በመሆኑ መሰል ውይይቶች ለታለመው ግብ መምታት አስፈላጊ መሆናቸው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የምክክር መድረኩ  የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች፣ የባለስልጣኑ የቦርድ አመራር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የዴሞክራሲ ተቋማት የበላይ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም