የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ሂደት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገለጸ

110

አዲስ አበባ መስከረም 14/2013 የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሰብአዊ መብትን በማስከበርና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ሂደት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገለጸ። 

ጠቅላይ አቃቤ ህግ  በ2013 በጀት ዓመት ለማከናወን ባቀዳቸው ተግባራትና በአስር አመት መሪ እቅዱ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

በመድረኩም የህግ አወጣጥና አተገባበር፣ የሰብአዊ መብትና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።

በጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ጉዳይ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ አሰግድ አያሌው እንዳሉት በ10 አመቱ መሪ እቅድ ውስጥ በአምስት አመት ውስጥ አዲስ ህግ የሚወጣላቸውና የሚሻሻሉ ህጎች ጥናት ይደረጋል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱም ይሁን በመሪ እቅዱ የሰብአዊ መብትን የማስከበርና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልም ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ እንዳሉትም የቀጣይ ትኩረቶች አዳዲስ ህጎችን ማውጣት፣ የሰዎች መብት ማስከበርና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መግታት ትኩረት ይደረግባቸዋል።

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና በወንጀል ላይ የሚሳተፉ አካላትን ወደ ህግ ለማቅረብም የተጠናከረ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

ለዚህም ስኬት የባለድርሻ አካላት ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት መካከልም የህግ የበላይነት እንዲከበር የሚሰራው ስራ መልካም መሆኑንና ቅንጅታዊ አሰራርም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሚሰራቸውን ስራዎች እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከተወካዮች ምክርቤት የህግና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከዴሞክራሲ ግንባታ ተቋማት እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም