የሀድያና ኦሮሚያ ህዝቦችን አንድነትና ትስስርን የሚያጠናክር የምክክር መድረክ በሆሳዕና ተካሄደ

83

ሆሳዕና ኢዜአ መስከረም 14/2013 ቀድሞ የነበረውን የሀድያና ኦሮሚያ ህዝቦችን አንድነትና ትስስር የበለጠ በማጠናከር በጋራ ለልማት እንዲውል ለማድረግና ለተተኪው ትውልድ መልካም እሴትን ለማውረስ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትሯ ገለጹ።

ሚንስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ማምሻውን እየተካሄደ ባለው የሁለቱ ብሄረሰብ ህዝቦች የትስስርና የአንድነት መድረክ ላይ እንዳሉት ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የቆየ አንድነትና አብሮነት ያላቸው ናቸው።

ኢትዮጵያውያን አንዱ ለአንዱ ደራሽ እርስ በእርስ የሚረዳዱ የሚተጋጋዙና በጋራ በፍቅር የመኖር የቆየ እሴት ባለቤት እንደሆኑም ገልጸዋል።

"አንዳንድ አካላት ለፖለቲካ መጠቀሚያቸው ሲሉ ዜጎች በኖረ የመረዳዳት የመተሳሰብና የመተጋገዝ ባህላቸውን እንዳይቀጥሉ የመለያየት ስራ እየሰሩ ይገኛሉ" ብለዋል።

የነዚህን አካላት ተገቢ ያለሆነ ተግባር ለማክሸፍ የህዝቦችን ትስስር በማጎልበት የመደጋገፍ የመተባበር ባህልን በማጠናከር አንዱ ለራሱ የሚያስፈልገው ለሌላውም እንደሚያስፈልገው በመረዳት በልዩነት ውስጥ አንድነትን አጠናክሮ በማስቀጠል መሄድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ስለዚህ የሀድያና የኦሮሞ ህዝብ የቆየ አንድነቱንና ትስስሩን በማጠናከር ለሀገር ልማትና አንድነት በጋራ መቆም እንዲችሉ መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት ትስስራቸውን ማስቀጠል እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ ባልቻ በበኩላቸው “ሁለቱ ህዝቦች በባህልና በቋንቋ ተቀራራቢ የሆነ እሴት እንዳላቸው ጠቁመው የህዝብ ትስስራቸውን በማጠናከር በሀገሪቱ አንድ የተሻለ ምዕራፍ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መድረኩ ትልቅ ፋይዳ አለው” ብለዋል።

የህዝቦችን አንድነት በማጎልበት በእንድም በሌላም ሁኔታ ሀገርን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን አጀንዳ ማፍረስና ሁሉም በየአካባቢው የሚገኘውን ሀገር አፍራሽ ኃይል አደብ እንዲገዛ ማደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሀድያ ብሄር የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ገራድ መንገሻ ሂቤቦ እንደገለጹት የሁለቱ ብሄሮች የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ ቀድሞም የነበረና በአንድነት ማህበራዊ ህይወቱን ምንም ነገር ሳይገድበው ሲከውን የነበረ ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ ህዝቦች በተለያዩ አካላት ሴራ እንዲለያዩ ተደረጎ እንደ ነበር አስታውሰው “አሁን ላይ የቀድሞ ግንኙነት መጀመሩ ጠቀሜታዉ የጎላ ነው” ብለዋል፡፡

"አንዳችን ከሌላችን ልዩነት የሌለን ህዝቦች ነን" ያሉት የኦሮሞ አባ ገዳ መግራ ለገሰ “ነባር ባህላችንን በማስቀጠልና ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ አብሮነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ማስቀጠል ተገቢ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም