ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስኬት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበራከትና ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

74

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2013 ( ኢዜአ) ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስኬት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበራከትና ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ገለጸ። 

ባለስልጣኑ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የልማት ተግዳሮት ላይ ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ከክልሎች የዘርፉ አስፈጻሚዎች ጋር የ2012 በጀት አፈጻጸምና የቀጣይ 2013 በጀተ አመት እቅድ ላይ ተወያይቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በወቅቱ እንደተናገሩት "ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ለሚደረገው ጥረት የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የላቀ ድርሻ አላቸው።"

ከአራት አመታት በፊት 9 ሺህ የነበሩት የአነስተኛና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች አሁን ላይ ከ20 ሺህ በላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

ኮቪድ 19 በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ የገለጹት ሃላፊው ወረርሽኙ ስጋት ብቻ ሳይሆን አጋጣሚዎችን ይዞ እንደመጣ አብራርተዋል።

በሽታው በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች በስፋት የታዩበትና የሀገር በቀል ምርቶችን በብዛት መጠቀም የተጀመረበት በመሆኑ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ኦላኒ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም እና ነባር ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ለ89 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

በአዲሱ በጀት አመትም አዳዲስ እና ነባር ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ለ140 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 62 ሺህ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም በእቅድ መያዙን ተናግረዋል።

በተያያዘም ባለስልጣኑ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ የልማት ተግዳሮቶች ላይ ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

በጥናቱ ኢንዱስትሪዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት እና በስራ ላይ እያሉ የሚገጥማቸው ተግዳሮቶች ይፋ ተደርገዋል።

በዚህም የማምረቻ ቦታ አለማግኘት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ማነስ እና በቂ መነሻ ካፒታል አለመኖር ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል ።

በጥናቱ የጥሬ እቃ ችግር ዋነኛው የኢንዱስትሪዎች ተግዳሮት እንደሆነም ተመልክቷል።

ጥናቱ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን ያቀረበ ሲሆን የኢንዱስትሪዎች ግብአት አቅራቢ ድርጅት አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁሟል።

የብድር ዋስትና ፈንድ በማቋቋም በሁሉም ባንኮች ኢንዱስትሪዎችን በተለየ ሁኔታ ሊያስተናግድ የሚችል አሰራር መዘርጋት እንዳለበትም በጥናቱ ታይቷል።

በመድረኩ ጥናቱን አስመልክቶ የተሰጡ አስተያየቶችን በመውሰድና በማዳበር በቀጣይ ጥናቱን ሙሉ ለማድረግ ይሰራልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም