ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ተረከበ

365

ፍቼ፣ መስከረም 14/2ዐ13 (ኢዜአ) ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ሊባኖስ ወረዳ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ትናንት ተረከበ፡፡

ትምህርት ቤቱን ለዩኒቨርሲቲው ያሰረከቡት የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ፀጋዬ ኃይሉ ናቸው።

ኃላፊው በወቅቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በወረዳው ሸረሮ ከተማ የተረከበው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀደም ሲል በመሰናዶ ትምህርት ቤትነት  ሲያገለግል የነበረ ነው።

ትምህርት ቤቱ 42ዐ ተማሪዎችን በአዳሪና ተመላላሽ በመደበኛነት ለማስተማር የሚያስችለውን ቁሳቁስና በጀት በማሟላት ዘንድሮ ስራ እንደሚጀምር ተመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ዶክተር ፀጋዬ ደዮ በተረከቡት ትምህርት ቤት ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ክፍል በከፍተኛ ውጤት የሚያልፉ ተማሪዎችን ከዞኑ 13 ወረዳዎች ተቀብለው እንደሚያስተምር ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ በቂ ቤተ መፃሕፍት፣ ቤተ ሙከራና ሌሎች ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ስራዎችን በማከናወን  ለሌሎች ትምህርት ቤቶች አርአያ ተደርጎ  እንደሚመቻች ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተጨማሪም ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስን በመከላከል በትምህርታቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ ሶስት ሚሊዮን 200ሺህ ብር  ግምት ያለው የማመሳከሪያ መፃሕፍትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ  ለዞኑ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቅርቡ መስጠቱንም አስታውሰዋል፡፡

የሚደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን በመጠበቅ በስነ ምግባር የታነፀ ስራ ወዳድ ትውልድ ለማፍራት  መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዞኑ ይህን መሰል ትምህርት ቤት ከፍቶ አገልግሎት መስጠቱ ለዞኑ ደግሞ ጎበዝ ተማሪዎች ትልቅ እድል መሆኑን የገለፁት የዞኑ ወላጅ መምህራን ህብረት አባል ወይዘሮ ሌሊሴ ባልቻ ናቸው፡፡

ተማሪዎች በተፈጠረላቸው ምቹ እድል ለመጠቀም በርትተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት የሰጠው የሸረሮ ከተማ  የስድስተኛ ክፍል ተማሪ መገርሣ ሁንዴ ዩኒቨርስቲው የተረከበው ትምህርት ቤት በተሻለ አቅምና ቁሳቁስ  ተደራጅቶ የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ  እንደሚያግዛቸው ገልጿል፡፡

ሰላሌ ዩኒቨርስቱ በማህበረሰብ አገልግሎት ለአካባቢው ነዋሪዎችና ተማሪዎች የሚጠቅሙ ኘሮጀክቶች ነድፎ ዘንድሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ከዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም