የሀሰተኛ ሰነድ ሲያዘጋጅ የነበረና ልብስ አስመሰሎ የኮባ ቅጠል ሲሸጥ የተገኙ ግለሰቦች በኅብረተሰብ ጥቆማ ተያዙ

122

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ በኅብረተሰብ ጥቆማ ተይዞ በምርመራ እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

በሌላ በኩል በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አልባሳት አስመስሎ የኮባ ቅጠል እየጠቀለለ ሲሸጥ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ሀሰተኛ ሰነዶቹ የተያዙት ፖሊስ የፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ልዩ ቦታው አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ  መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

በሀሰት የተዘጋጁ ፓስፖርቶች፣ ማኅተሞች፣ ቲተሮች፣ የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎችና የዝሆን ጥርስ ከነተጠርጣሪው ሊያዙ መቻላቸውን የጉዳዩ መርማሪ ዋና ሳጅን አብድልካሪም አህመዲን ተናግረዋል።

አካባቢው በመልሶ ማልማት ላይ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ እንደሚስተዋልበት የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እዮብ ተከተል ገልጸዋል።

አያይዘውም የልማት ሥራውን ለማከናወን ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በአፋጣኝ ወደ ሥራ በመግባት አካባቢውን ከሕገወጦች መከላከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል በሀገርና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ኅብረተሰቡ በዚህ ድርጊት ላይ የሚሳተፉ አካላትን አጋልጦ እንዲሰጥም ኃላፊው ጠይቀዋል።

ኅብረተሰቡ ሕገወጥነትን በመከላከል የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ኢንስፔክተር እዮብ ተከተል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮንትሮ ባንድ የገቡ የተለያዩ የሺሻ ዕቃዎችን በሕዝብ ጥቆማና ባደረገው ጥናት መያዙን የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ አስታወቋል።

የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ ዓለሙ እንደገለጹት ሺሻ ለማጨስ ጥቅም ላይ የሚውሉ በርካታ የተለያዩ ዕቃዎችን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት ጥቆማ በቀረበበት ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ይዞ በምርመራ እያጣራ ይገኛል።

እነዚህ ዕቃዎች በኮንትሮባንድ ገብተው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በሽያጭ የሚከፋፈሉ መሆኑን  ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አልባሳት አስመስሎ የኮባ ቅጠል እየጠቀለለ ሲሸጥ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር የዋለው ልዩ ቦታው ዘነበወርቅ አካባቢ ልብስ ነጋዴ በመምሰል በአንደኛው ፔስታል የኮባ ቅጠል በሌላኛው ደግሞ የተለያዩ አልባሳቶችን ይዞ እንደሚንቀሳቀስ የወንጀሉ መርማሪ ረዳት ሳጅን ሀብታሙ ባለህ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው ጌለሰብ አልባሳት ከገዙት በኋላ የኮባ ቅጠል የያዘውን ፌስታል በድብቅ ቀይሮ በመስጠት በርካቶችን ሲያታልል እንደነበር የምርመራ መዝገቡን ዋቢ አድርገው መርማሪው ተናግረዋል፡፡

የአካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ረዳት ሳጅን ሀብታሙ ባለህ በተለይም በበዓላት ወቅት እንደዚህ አይነት ወንጀሎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ማንኛውንም ዕቃ ሲገዛ ይዞ ከመሄዱ በፊት ማረጋገጥ እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም