የስካውት ማኅበር አባላት ከ150ሺ ሰዓት በላይ ኮሮናን የመከላከል አገልግሎት ሰጥተዋል

101

መስከረም 14/2013(ኢዜአ) የስካውት ማኅበር አባላት ከ150ሺ ሰዓት በላይ ኮሮናን የመከላከል አገልግሎት መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር አስታወቀ፡፡

ከተመሰረተ አንድ መቶ አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር 86ኛውን የኢትዮጽያ ስካውት ቀን አክብሯል፡፡

በስካውት ማህበሩ የስራ አስፈጻሚ  ኮሚሽነር አቶ  ብሩክ መሰለ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር አባላት ባሳለፍነው ዓመት በተለያዩ ማህበራዊ ተግባራት ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ስካውቶቹ ከህብረተሰባችን ጎን መቆም አለብን በሚል በመላው ኢትዮጵያ በሽታውን በመከላከልና ግንዛቤ በመስጠት ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

ስካውቶቹ በሚሳተፉበት የነጻ አገልግሎቶች ሰዎች የእጆቻቸውን ንጽሀና እንዱጠብቁ ፤ ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ ግንዛቤ ሰጥተዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት ወቅት ደግሞ ከጸጥታ አካለት ጋር በጋራ በመሆን ሰዎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁና ማስክ እንዲለብሱ በማስተማር በመላው አገሪቱ መንቀሳቀሳቸውን ነው የገለጹት፡፡

ኮቪድን በመከላከል ስራ ላይ የሚያገለግሉ ማስታወቂያዎችን በመስራት፤ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ፤ በመለጥፍ  10ሺ የማህበሩ አባላት ከ150 ሺ ሠዓት በላይ የነጻ አገልግሎት መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የስካውቱ አባላት በሶስት መቶ ስካውቶች መሪነት ያከናወኑት ተግባርና የሰሩበት ጊዜ ተደምሮ የአለም የስካውቶች ማኅበር ከ150ሺ ሰዓት በላይ የነጻ አገልግሎት መስጠታቸውን እንዳስታወቀ ያስረዱት ደግሞ የማህበሩ አባል ወይዘሮ አይናለም ጌጤ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ኮቪድ በተከሰተበት ጊዜ ብሔራዊ የደም ባንክ ያስተላለፈውን አገራዊ ጥሪ ተከትሎ ከ130 በላይ ስካውቶች ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ችግኞችን የመትከል ተግባርም የስካውት ማኅበሩ አባላት ሌላው የተሳተፉበት ስራ ነው፡፡

በሌላ በኩል መንግስት የማህበረሰብ ስብዕና ግንባታ ስራዎችን ለማከናወን በሚያስብበት ጊዜ እንደ ስካውት ማህበር ካሉ  የሲቪል ማህበራት ጋር ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት አለበትም ሲሉ የስካውት ማህበሩ ኮሚሽነር አቶ ብሩክ መሰለ  አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም