ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ ጀዋር መሃመድ ክስን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

57

አዲስ አበባ መስከረም 14/2013(ኢዜአ) ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ ጀዋር መሃመድ ክስን ለመስማት ለመስከረም 21 ቀን 2013 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡

ተከሳሾቹ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 1ኛ የህገ-መንግስትና ጸረ-ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱን በመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ባለመቅረባቸው ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አያያዝ ለመከታተል ስለሚያመቸው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ወስኗል፡፡

ከዚህ በፊት ተከሳሾቹ በፌደራል ፖሊስ ጥበቃ ስር እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት መውረዳቸው ቤተሰብ እንዲጠይቃቸውና ከጠበቆች ጋር እንዲገናኙ አመቺ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን አሳልፏል፡፡

በተጨማሪ የተሟላ ህክምና ለማግኘት በማረሚያ ቤት መቆየታቸው አመቺ ነው ተብሏል፡፡

5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ደግሞ ፍርድ ቤት ያልቀረቡበትን ምክንያት የማረሚያ ቤት ፖሊስ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

ሁኔታዎች ለጥበቃና ለህክምናም የተሻለ በመሆኑ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩም ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተሰማን የምስክር ቃል ከክስ መዝገብ ጋር አለመያያዙን በመግለጽ እንዲያያዝ የቀረቡትን አቤቱታ በቀጣይ ቀጠሮ ብይን እንደሚሰጥበትም ገልጿል፡፡

በውጭ አገር የሚገኙ ተከሳሾችን ፖሊስ ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ያልቀረቡ ተሳሾችን ፖሊስ እንዲቀርብም ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግና ጠበቆች ላቀረቡት አቤቱታ በሚቀጥለው ቀጠሮ ብይን እንደሚሰጥም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም