የከተሞችን የውሃ አገልግሎት ስርዓት የሚያሻሽል ፕሮጀክት በወተር ኤይድ ኢትዮጵያ ይፋ ሆነ

129

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2013 ( ኢዜአ) የከተሞችን የውሃ አገልግሎት ስርዓት የሚያሻሽል ምእራፍ ሁለት ፕሮጀክት በወተር ኤይድ ኢትዮጵያ ይፋ ሆነ። 

ወተር ኤይድ ኢትዮዽያ ምእራፍ ሁለት የከተማ ውሃ፣ ንፅህና እና ስነጽዳት ስርዓት ማጠናከርያ’ የተሰኘ የከተሞችን የውሃ አገልግሎት የሚያሻሽል ፕሮጀክት በይፋ አስጀመረ።

በምእራፍ ሁለት በ3 ክልሎች በሚገኙ 23 ኩታ ገጠም አነስተኛ ከተሞችን የሚያቅፍ መሆኑም ታውቋል።

ለፕሮጀክቱ ትግበራ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት ሲሆን በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ይከናወናል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ኩታገጠም አነስተኛ ከተሞችን በአንድ የዞን ዋና ከተማ የማስተባበር አካሄድ የሚከተል ሲሆን በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በመተግበር የውሃ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ይሰራል።

በምእራፍ አንድ ከ2006-2011 .ም በ20 ክተሞች በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ወተርኤይድ ኢትዮዽያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የፕሮጀክቱን ወጪ በከፊል የሚሸፍነው በብሪታንያ የሚገኘዉ ዮክሻየር ወተር የተባለ የግል ኩባንያ የሚሸፍነው መሆኑም ታውቋል።

የወተርኤይድ ኢትዮዽያ ካንትሪ ዳይሬክተር ያእቆብ መተና እንደተናገሩት“ወተርኤይድ-ኢትዮዽያ በሃገሪቱ ባሉ ክተሞች የውሃ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።

ድርጅቱ ገንዘብ በማሰሰባሰብና ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የውሃ፣ ንጽህና እና የጽዳት ፕሮግራሞችን በመቅረጽ የከተሞችን የውሃ አገልገሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ማህበርስቡን ንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል።

በበይነ መረብ ፕሮጀክቱ ይፋ ሲደረግ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚንስቴርና  የጤና ሚንስቴር ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የክልል የውሃ ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም ከወተርኤይድ ዩኬና ከምስራቅ አፍሪካ ወተርኤይድ ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት እንደታደሙበትም ታውቋል።

በኢትዮጵያ ከ10 ሰዎች መካከል አራቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅረቦት እንደማያገኙ የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም