ከፍተኛ ትምህርትን ማስቀጠያ መርሃ ግብር "በፕሮጀክት" መልክ ይተገበራል ተባለ

98

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2013 ( ኢዜአ) በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት የማስቀጠል ሂደት "በፕሮጀክት" መልክ የሚተገበር መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሰሞኑን በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየተከላከሉ ትምህርት እንዲቀጥሉ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ተገምግሟል።

በውይይቱ ላይ የ45ቱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች የተሳተፉ ሲሆን የተወሰኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳሉት ትምህርት ማስቀጠያው በልዩ ሁኔታ በ'ፕሮጀክት' ይምራል ብለዋል።

የወረርሽኙ ጉዳት ቀላል አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ አቅም በማሰባሰብ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሰተባበር በልዩ ሁኔታ የሚመራ ይሆናል ብለዋል።

ሚኒስቴሩን ጨምሮ ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ ጉዳዩን በአግባቡ እንዲረዳውና በጥንቃቄ እንዲጓዝ ለማድረግ ራሱን ችሎ በፕሮጀክት መልክ ይከወናል ነው ያሉት።

ለመምህራን፣ ለተማሪዎችና ለሰራተኞች አስፈላጊው የመከላከልና ጥንቃቄ ተግባራት ተደርገውበት የትምህርትና ስልጠና ተግባር እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።


ለሁለት ቀናት በቆየው ውይይት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በመጠኑም ቢሆን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያነት ሲያገለግሉ በመቆየታቸው የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል።

በጥቅሉ ወረርሺኙን ለመካለከል የሚረዳ መጠናኛ እድሳትና ጥገና ካደረጉ በኋላ ትምህርት መጀመር እንደሚቻል መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የደረሱበትን የዝግጅት ደረጃ ለሚኒስቴሩ ሪፖርት ካደረጉና ሚኒቴሩም ይህንን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የ2012 ዓ.ም የመጨረሻ ዓመት ተመራቂዎችን ቅድሚያ ሰጥቶ ማስመረቅ ቀዳሚ ተግባር ሲሆን የቀሪዎቹ ጉዳይ ደግሞ በሂደት ይወሰናል ብለዋል።

ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ከ750 ሺህ በላይ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ እና 600 ሺህ የሚደርሱ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችን ትምህርት እንዲያቋርጡ አድርጓል።

እነዚህን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ መንግስት የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን እየተከተለ መሆኑ ተገልጿል።

ወረርሽኙ በዓለም ላይ 78 ሚሊዮን የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ከትምህርታቸው ማስተጓጎሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም