በጎርፍና ናዳ ሰብል ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ተተኪ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ ነው

68

ባህርዳር መስከረም 14 /2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በጎርፍ፣ በረዶና በመሬት መንሸራተት ሰብል ለወደመባቸው 17 ሺህ 800 አርሶ አደሮች ተተኪ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ሰጪ ዳይሬክተር አቶ ጀምበሩ ደሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የክረምት ወቅት ዝናብ ተከትሎ በጎርፍ ፣ በበረዶና በመሬት መንሸራተት በ24 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል ወድሟል።
የወደመውን የአርሶ አደሮች ማሳ በዘር ለመተካት 11 ሺህ 481 ኩንታል የሽብራ፣ ጓያ፣ አጃና ሌሎች ሰብሎች ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ለክልሉ ግብርና ቢሮና ለፌዴራል የሚመለከታቸው አካት የዘር አቅርቦት ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል ።
ምላሹ እንደተገኘ አርሶ አደሮቹ ዘሩን በመጠቀም ፈጥነው ማሳቸውን እንዲሸፍኑ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች የተጠየቀን ተተኪ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥያቄውን መሰረት በማድረግ ችግሩን የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች መላኩን ገልጸዋል ። 
ቡድኑ በሚያቀርበው የማረጋገጫ የጥናት ውጤት መሰረት ለየስነምህዳሩ ተስማሚና ፈጥኖ የሚደርስ ዘር እንደሚቀርብ አመላክተዋል ።
በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የዋገጠራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንዴ አለበል በመኽር ወቅት በአንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸው ላይ ያለሙት የሩዝ ሰብል በጎርፍ የወደመባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
"በክረምት ጎርፍ የሚከሰት ቢሆንም የዘንደሮው የከፋ ነው" ያሉት አርሶ አደር ወንዴ ካለሙት የሩዝ ማሳ 90 ኩንታል ምርት ይጠብቁ እንደነበር ገልጸዋል።
በጎርፍ ክስተት ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ መርጌታ ተቀባ መንግስቱ ናቸው።
አሁን ላይ ማሳቸው ያለአገልግሎት መቀመጡን የገለጹት አርሶ አደሮቹ የዝናቡ ጊዜ ሳያልፍ የዘር ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም