ሚኒስቴሩ ዕድገትን ለማረጋገጥ በመጠጥ ውሃ፣ መስኖ ልማትና ኢነርጂ ላይ እየሰራ ነው

116

አዳማ መስከረም 14/2013(ኢዜአ) ቀጣይነት ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በመጠጥ ውሃ፣ መስኖ ልማትና ኢነርጂ ላይ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የቀጣይ አስር ዓመት የተያዘው በጀት ዓመት ዕቅዱን ለማዳበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መገምገም ጀምሯል።

በግምገማው  መድረክ  የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶከተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንደገለፁት የማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በተለይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ መስኖ፣ ኢነርጅና የንፁህ መጠጥ ውሃ ወሳኝ ናቸው።

በዚህም የንፁህ መጠጥ ውሃ አሁን ካለበት 66 በመቶ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል።

የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ከውጭ የሚገባውን ስንዴን በሀገር ውስጥ መተካትና ለግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬን ማዳን የዕቅዱ አካል እንደሆነም ተናግረዋል።

የኃይል አቅርቦት ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረው የልማት ሂደት የተጓተተ ከመሆኑም ባለፈ ሀገራዊ ሽፋኑ 45 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ሁኔታ የተጀመረውን  ልማት በሚፈልገው መልኩ ማስቀጠል አይቻልም ብለዋል።

ዕቅዱ ከሀገራዊ  የመልማት ፍላጎት ጋር የተቃኘ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከ21 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በገጠርና በከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተመሳሳይ ከ4ሺህ 400 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም መፈጠሩን አውስተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ባለው የግምገማው መድረክ   ሚኒስትሩ  ባቀረቡት የቀጣይ አስር  ዓመት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሴክተር ዕቅድ ዙሪያ  ውይይት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም