በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ለሴቶች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድል እንዲፈጠር ተጠየቀ

143

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2013 ( ኢዜአ) የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማሳደግ ለሴቶች የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚያሰስፈልግ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች።

በ75ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ የቡድን 7 እና የአፍሪካ አገራት የተሳተፉበት በቪዲዮ የታገዘ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንዳሉት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማሳደግ ለሴቶች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድል መፍጠር ይገባል።

በፓናሉ የኔዘርላንድስ ንግሥት ማክሲማ፣ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የፈረንሳይ ፋይናንስ ኢኮኖሚ እና ድጋፍ ሚኒስትር፣ የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን መሰራች ሚሊንዳ ጌት ተገኘተዋል፡፡

የፓናል ውይይቱም ትኩረት የነበረው በአፍሪካ ዲጂታል ፋይናንስን በማጠናከር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነበር።

ዶክተር ኢዮብ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የአፍሪካ መንግስታት ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ በመገንባት ብሎም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ብዙ እየሰሩ ቢሆንም ሴቶችን በዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ብዙ ይቀራቸዋል፡፡

በተለይም ደግሞ በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራት ያለባቸው የተቀናጁና ተከታታይ ተግባራት እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

የሴቶች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነት እና አጠቃቀም ማሻሻል በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶችን ህይወት አንድ ደረጃ ወደ ፊት የሚያራምድ አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ 

በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት አስፈላጊነት የጎላ ሚና እንዳለው ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በታዳጊ ኢኮኖሚ ላይ የሚገኙ ሀገራት ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ የሚገጠሟቸውን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፋይናንስ ማካተት ዓላማዎችን በማራመድ ተጨማሪ ዕድሎችን ለህዝባቸው ማምጣት ችለዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በፋይናንስ ሴክተር ላይ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ብትሆንም፣ ለአብዛኛው የህብረሰተስብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎቱ ተደራሽ እንዳልሆነም ገልፀዋል፡፡

ይህንኑ ችግር ለመፍታት መንግስት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ቀረጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አብራርተዋል። 


መንግስት ተንቀሳቃሽ የባንክ ወኪሎች አሰራር መመሪያ በማዘጋጀት፣ የብሄራዊ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለመፍጠር የሚያስችል ስትራቴጂ በመቀየስና አካታች የፋይናንስ ስትራቴጂውን የመከለስ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ 

በዚህም ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የፋይናንስ ቴክኖሎጂውን አገልግሎት በከፍተኛ ፍጥነት በማስፋፋት የአገልግሎቱ ተደራሽነት ይጎለብታል ሲሉም አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ላይ የአካታች ፋይናንስ ግቦችን ለማሳካት ተገቢ የሆኑ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተነስቷል። 


መድረኩ ከተጠናቀቀ በኋላ ዶክተር እዮብ  ከተባበሩት መንግስታት አካታች የልማት ፋይናንስ ዋና ጸሀፊ ልዩ መልዕክተኛ ንግስት ማክሲማ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ሁሉንም ተደራሽ የሚያደርግ የፋናንስ አቅርቦት ለመዘርጋት እያካሄደች ያለውን ጥረት አብራርተዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛዋና አጋሮቻቸው በፋይናንስና በተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎችና የድጋፍ ፕሮግራሞችን በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን እገዛና አጋርነት ዶክተር እዮብ አድንቀው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም