መንግስት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልን የሰላም ቀጣና ለማድረግ በትኩረት ይሰራል…አቶ ደመቀ መኮንን

56

ባህር ዳር መስከረም 14/2013(ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሁን ካለበት የፀጥታ ችግር ተላቆ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ቀጠና እንዲሆን መንግስት ጠንካራ ህግ የማስከበር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ የደረሰውን የፀጥታ ችግር የፌዴራልና የሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በግልገል በለስ ከተማ ውይይት መካሔዱ ይታወሳል።

ይሔንኑ በሚመለከት መስከረም 10/2013 ኢዜአ ባስተላለፈው ዘገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ያልተገለጸ መልዕክት እሳቸው እንደገለጹ ተደርጎ በመተላለፉ ለተፈጠረው ስህተት ኢዜአ ይቅርታ እየጠየቀ ትክክለኛውን ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ የደረሰውን የፀጥታ ችግር የፌዴራልና የየሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በግልገል በለስ ከተማ ትናንት ውይይት ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የቤንሻንጉል ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ የግድቡን መጠናቀቅ የማይፈልጉ የውስጥና የውጪ ሃይሎች በየጊዜው ክልሉን ለማተራመስ እየሰሩ ይገኛሉ።

“የቀጠናውን መረጋጋት የማይፈልጉ ቡድኖች በአካባቢው የተደራጁ ሃይሎችን በመጠቀም ለዘመናት በጋራ ተባብረውና ተዋደው በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠር ፍላጎታቸውን ለማሳካት እየሰሩ ነው”ብለዋል።

የሰሞኑ ድርጊት ብሄርን መሰረት ያደረገ ሳይሆን የቀጠናውን መረጋጋት በማይፈልጉ ሃይሎች ድጋፍ በሚደረግላቸው ቡድኖች የተፈጠረ ድርጊት መሆኑን ገልጸው በድርጊቱ የተሳተፉ ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል።

የፌዴራል መንግስት ቀጠናውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከብጥብጥ የነጻ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

“የመተከል ዞን የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብቱንና እውቀቱንና ሃብቱን በማፍሰስ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት የህዳሴውን ግድብ እየገነባበት የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ጠላት በክፉ አይኑ የሚመለከተው ነው” ብለዋል።

በችግሩ እጃቸውን አስገብተው በድርጊት የተሳተፉ ቡድኖችንና ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላትን በመለየት ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በነገው እለት የፌዴራል መርማሪ ቡድን ወደ አካባቢው እንደሚያቀናም አስገንዝበዋል።

“ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የእለት ደራሽ እርዳት መሰጠትና ወደ ነበሩበት ቦታ ተመልስው ያለ ስጋት እንዲኖሩ የማድግ ስራም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው እንደተናገሩት በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ አይጋሊና ኤጳር ቀበሌ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር አሳዛኝና ሊደገም የማይገባው ጉዳት ደርሷል።

ለችግሩ መከሰትና የጉዳት መጠኑ እንዲሰፋ በማድረግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት እንዳሉበትም ገልጸዋል።

ድርጊቱን የፈጸሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሽፍታና አሸባሪ ሃይሎች ሲሆኑ በውስጥና በውጪ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የአካባቢው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ምቹ አለመሆን የክልሉ የፀጥታ ሃይል ፈጥኖ ድርጊቱን መከላከል እንዳልቻለ ጠቅሰው፤” የመከላከያ ሃይል ከገባ በኋላ አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላም ተመልሷል” ብለዋል።

“የመተከል ዞን የኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ መገኛ እንደመሆኑ መጠን የግድቡን መጠናቀቅ በማይፈልጉ ሀይሎች የተለያዩ አጀንዳዎችን እየተፈጠሩ ህዝቡን እርስ በእርስ ለማጋጨት ታቅዶ እየተሰራ ነው”ብለዋል።

“አካባቢው የመላ ኢትዮጵያዊያንን ትኩረት የሚሻ በመሆኑ የፌዴራል መንግስትን ልዩ ድጋፍ ይፈልጋል” ሲሉም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

በዞኑ በየጊዜው እየተፈጠረ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የአማራ ክልል ከፌዴራልና ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ናቸው።

“በተለይም በተደጋጋሚ ግጭት የሚነሳበት የመተከል ዞን ሆን ተብሎ የብሄር መልክ እንዲይዝ የሚደረገው የህዝቦች በጋራ መኖር ሰላም የማይሰጣቸው አካላት የሚጠነስሱት ሴራ ነው”ብለዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግስትም ችግሩን በመረዳት በተለይ በአጎራባች ወረዳዎች ላይ ከፌዴራልና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት ሰላምን የማስከበር ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በውይይት መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሩ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ ዓንዷለምና የአማራና የቤንሻንጉል ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም