በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን የሁለትዮሸ ግንኙነት ለማሳደግ ጠንክሬ እሰራለሁ - አምባሳደር ታን ጂያን

67

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን የሁለትዮሸ ግንኙነት ለማሳደግ በሄዱበት ሁሉ እንደሚሰሩ ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ገለጹ።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2017 ጀምሮ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታን ጂያን የመሰናበቻ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ በቆዩባቸው ሶስት ዓመትና በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማሳደግ ሲሰሩ እንደነበር ገልጸዋል።

''በኢትዮጵያ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር ከሚደረገው ጥረት ጀምሮ የተካሄደውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ በቅርበት ተመልክተናል'' ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የምታደርገው ሁሉን አቀፍ ለውጥ የጸና ይሆን ዘንድ ቻይና የማያቋርጥ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና በነጻና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት፣ በሰላምና መረጋጋት መስፈን እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ፣ ቀጣይነት ባለው የዘላቂ የልማት ግቦችና የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማስከበር ሁለቱም አገሮች የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የዘንድሮው 2020 ዓመት ኢትዮጵያና ቻይና  ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበት 50ኛ ዓመት መሆኑን ገልጸው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በቀላል ባቡርና በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ በጋራ መስራታቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ለአገሮቹ ሁሉን አቀፍ ግንኙነት መጎልበት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመው፤ ''የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ሁሉን አቀፍ ግንኙነት እንዲጎለብት በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ጠንክሬ እሰራለሁ'' ብለዋል።

የቻይና መንግስትና ህዝብ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል አምባሳደር ታን።

ኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት በማድነቅ፤ ''ቻይና ልምዷን በማካፈል እገዛ ታደርጋለች'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም