በሐረሪ ክልል ከ11 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው

85

ሐረር፣ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) በተያዘው የበጀት ዓመት ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር  አቶ ንጉሱ ጥላሁን የተመራ ሉኡካን  ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበትና ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ዛሬ ከሐረሪ  ክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት የዜጎችን የስራ እድል መፍጠር ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር ለሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው።

ለዚህም በክልሉ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመስሪያ እና ከመሸጫ ቦታ አቅርቦት ጋር በተያያዘም ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን በሚደረገው ርብርብ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ስራ እድል ፈጠራ  ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በተለይም ከብድር አመላለስና የስራ ባህልን ከማጎልበት አንፃር የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ያሉ እምቅ ሃብቶች በመጠቀም የዜጎችን ተጠቃሚነት ማጎልበት ላይም እንዲሁ፡፡

ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጎልበት ከወረዳ ጀምሮ በጋራ ተናቦ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ  በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ እያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ እቅዱን ለማሳካት ይሰራል ብለዋል፡፡

ከብድር አመላለስ ጋር ተያይዞም ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በተያዘው የበጀት ዓመት 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ የሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም