ለህብረተሰቡ ከመጉላላት ነጻ የሆነ የብር ኖት ለውጥ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል- ባንኮች

79

መቀሌ፣ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ ) በትግራይ ክልል የሚገኙ ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለህብረተሰቡ ከመጉላላት ነጻ የሆነ የብር ኖት ለውጥ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቁ።

በክልሉ የመንግስትና የግል ባንኮች እንዲሁም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአዲሱ የብር ኖት ለውጥ ሂደት ዙሪያ ዛሬ በመቀሌ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅና የባንኮች ፋይናንስ ፎረም ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ሰዋሰው በሰጡት መግለጫ አዲሱ የብር ኖት ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እንደሚያስቀር አስታውቀዋል።

''የብር ኖት ለውጡ ህዝባችን ኋላ ቀር ከሆነ የገንዘብ አያያዝና የግብይት ስርዓት ወጥቶ ወረቀት አልባ የዲጅታላይዜሽን አሰራር እንዲከተል የሚያደርግ እንጂ  የተለየ ጉዳት የለውም'' ብለዋል ።

ነባር የብር ኖቶችን በአዲሱ ለመቀየር የሚመጣ ተገልጋይ መጉላላት እንዳይደርስበት በክልሉ ከሚገኙ 120 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በተጨማሪ በየገበያ ስፍራዎች ጊዚያዊ የብር ኖት መቀየሪያ ጣቢያዎች ከፍቶ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል ።

በአንበሳ ዓለም አቀፍ ባንክ የሰሜን ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንትና የፋይናንስ ፎረም አባል አቶ አክሊሉ ሓየሎም በበኩላቸው የአዲሱ የብር ኖት ለውጥ እያንዳንዱ ተገልጋይ የቁጠባ ሂሳብ በመክፈት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል ።

የባንኮችን የገንዘብ አቅም የሚያጠናክርና የባለሃብቶችን በኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚያሰፋ እንደሆነም ጠቅሰዋል ።

በክልሉ በሚገኙ 134 ባንኮች ከመደበኛ የስራ ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ እስከ ምሽቱ 3፣00 ሰዓት የብር ለውጥ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።

"በየደረጃው ባሉ ቅርንጫፎች ተጨማሪ የሰው ሃይልና ኮምፒዩተሮችን በማሟላት ህብረተሰቡ ከመጉላላት ነጻ የሆነ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኝ እየሰራን ነው'' ያሉት ደግሞ የደደቢት ብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበር ስራ አስኪያጅና የፋይናንስ ፎረም አባል አቶ ሙሉጌታ ብርሃነ ናቸው።

"አንድ ብርም ቢሆን ሳይመነዘር ቢቀር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅእኖ ከባድ ነው" ያሉት አቶ ሙሉጌታ የክልሉ መንግስት ጉዳዩን በመገንዘብ ህዝቡ ነባር የብር ኖቶችን ወደ ባንክ በማምጣት በአዲሱ እንዲለውጥ በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

የትግራይ ክልል የኢኮኖሚ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ዶክተር መብራህቱ መለስ "ነባሩን የብር ኖት በአዲሱ መቀየር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው" ብለዋል።

የንግድ ዘርፍ ማህበራት፣ የወጣቶችና ሴቶች ማህበራት ጭምር አደረጃጀቶቻቸውን በመጠቀም ህብረተሰቡ ግራ ሳይጋባ ነባር የብር ኖቶችን በአዲሱ እንዲለውጥ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም