በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋሉ ህገወጥ ተግባራትን በማጥራት እርምጃ የመውሰድ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

77

አዲስ አበባ መስከረም 13/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋሉ ህገወጥ ተግባራትን በማጥራት እርምጃ የመውሰድ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባዋ ይህን ያሉት ዛሬ ከከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

በውይይቱ የተሳተፉት ነዋሪዎችም በከተማ አስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚደንቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም መፈታት ያለባቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የተለያዩ ህገወጥ ተግባራት በከተማዋ እየተስተዋሉ መሆኑን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለይ በታችኛው የከተማዋ መዋቅሮች ጎልተው እንደሚታዩ፣ ከመሬት ወራረና ከኮንዶሚነዬም ቤቶች ጋር በተያይዞ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው ፈጥነው እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በፍቅርና በአንድነት በሚኖሩት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ችግር የሚፈጥሩ ቡድኖች ስላሉ በእነዚህም ላይ መንግስት ተገቢ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

"ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ተግባራትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል" ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ተግባራት መኖራቸውን አምነው፤ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመሬት ወረራ፣ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁም ሰፋፊ የታጠሩ መሬቶችን አጥርቶ እርምጃ የመውሰድ ሥራ በቀጣይ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

ከዚህ በኋላ ከተማ አስተዳደሩ ሌብንት፣ ብልሹ አሰራር፣ ከህግ አግባብ ውጭ የሚደረግ የዋጋ ንረትንና መሰል ህገ ወጥ ታግባራትን እንደማይታገስም ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባዋ ገለጻ፣ በቀጣይ የህብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታ የሚያውኩ ተግባራትን በመከላከል የህግ ማስከበር ሥራዎች በትኩረት ይሰራሉ።

የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ከማረጋገጥ አኳያ ህብረተሰቡ የጽንፈኞችን እንቅስቃሴ እንዲታገልም ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ አቅርቧል።

አብሮነትና አንደነትን በትብበር በማስቀጠል የከተማዋና የአገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው " ለእዚህም በጋራ መስራት አለብን " ብለዋል።

"በህዝቦች መካከል ችግር እየፈጠሩ ያሉ ጽንፈኞች ህዝቡ በጋራ ሊታገል ይገባል፣ ስርዓት አልብኝነትን ለመከላከል በሚደረጉ ሥራዎች ውስጥ ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጥል አለበት" ሲሉም ጠቁመዋል።

ለዘመናት የተከመሩ የህዝብ ጥያቄዎችን በሂደት ለመመለስና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለማስቀደም አሰራር የመዘርጋት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም