የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ጥራት ያለው የዲጅታል ኢኮኖሚ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል --አቶ አህመድ ሺዴ

84

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተወዳዳሪ፣ ተደራሽና ጥራት ያለው የዲጅታል ኢኮኖሚ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ተናገሩ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድርና ከፊል ሽያጭ ማቅረብን አስመልክቶ ከግልና ከመንግስት ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም ያለ ተወዳዳሪ ዲጂታል ኢኮኖሚ ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ተነስቷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተወዳዳሪ፣ ተደራሽና ጥራት ያለው የዲጅታል ኢኮኖሚ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድርና ከፊል ሸያጭ መቅረቡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሥራ እድልና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለመፍጠር እንዲሁም አገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው የገለጹት፡፡

"ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባላት አገር ተወዳዳሪ የቴሌኮም ዘርፍ መፍጠር ይገባል" ያሉት አቶ አህመድ፤ ዘርፉን ወደ ግል ለማዞር የተጀመረው ስራም ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ዘርፉ ለውድድርና ከፊል ሽያጭ ክፍት መደረጉ ዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓትን መገንባት ዓለማ በማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የዘርፉን ተደራሽነት ለማሳለጥና ለዜጎችም ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የተወዳዳሪነት መንፈስን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

"አዳዲስ ተወዳዳሪ ተቋማት የዲጂታል ኢኮኖሚውን እንዲቀላቀሉ መታሰቡ ኢትዮ-ቴሌኮም ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችል ያደርገዋል"  ብለዋል፡፡

"እየተጠናቀቀ ያለው የ10 ዓመት አገራዊ የልማት ዕቅድ ተግባራዊ ሲደረግ ሃብትን በፍትሃዊና በግልጽነት ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ሰፊውን ድርሻ ይይዛል" ያሉት ደግሞ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ናቸው፡፡

ዘርፉ አገሪቱ በየዓመቱ የምታመርተውን የሰው ኃይል በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ እድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም አስረድተዋል፡፡

ሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች ዘርፍን ለመቀላቀል በአሁኑ ወቀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ ቴሌኮምንና ተያያዥ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ማዘመን ከሌሎች ዓለማት ጋር በቀላሉ ለመገበያየትና ዘመናዊ የባንኪንግ ስርዓትን ለመዘርጋት የራሱ ፋይዳ አለው፡፡

ቴሌኮምን ለውድድርና ከፊል ሽያጭ ከፍት ማድረጉ የባንኮችን ሥራን ለማገዝ የማይተካ ሚና እንደሚጫወትም ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ላይ ከአገራዊ ተጠቃሚነት፣ ከብሔራዊ ደህንነት፣ ከህግና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ከጥራትና ተደራሽነት፣ ከፈቃድ አሰጣጥና ጨረታ ሂደት፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከምሁራኑ ለተነሱት ጥያቄዎች በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በፕላን ኮሚሽን እና በኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ዘርፉ ለውድድርና ከፊል ሽያጭ ክፍት መደረጉን ተከትሎ 12 የቴሌኮም ድርጅቶች የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያውን ምላሽ እንዳስገቡ ታውቋል፡፡

ውድድሩና ከፊል የኢትዮ-ቴሌኮም ሽያጩ ከመጪው ጥቅምት እስከ የካቲት ባሉት ወራቶች ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም