በሀገሪቱ መደበኛ የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር የተቀናጀ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ይተገበራል --ጤና ሚኒስቴር

145

ሀዋሳ፣ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በመደበኛው የጤና አገልግሎት ላይ የተፈጠረውን ችግር በማቃለል ዘርፉን ለማጠናከር የተቀናጀ የጤና ዕቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ የተመራው ሉኡካን ኮሮና  በመደበኛው የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫናና የቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ በሲዳማ ክልል የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

ዶክተር ደረጄ በዚህ ወቅት በተደረገው የመስክ ምልከታ የጤና ተቋማት መደበኛ የህክምና አገልግሎትና የኮሮና መከላከል ስራ ያሉበትን ደረጃ መመልከት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የጤና ተቋማትና አመራሮች ማህበረሰቡን በማስተባበር ቫይረሱ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል እያደረጉት ያለው ርብርብ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

ላለፉት ስድስት ወራት ከአመራር እስከ ባለሙያ ድረስ ወረርሽኙን መከላከል ላይ ትኩረት በመደረጉ በመደበኛ የጤና አገልግሎት ክፍተት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በማቃለል የዘርፉን ስራ ለማጠናከር ዘንድሮ ሚኒስቴሩና ጤና ተቋማት የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ዕቅድ አዘጋጅተው እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።

እቅዱ የጎርፍ ክስተት ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ወባና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንና እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ ተደርጎ በየሳምንቱም እየተገመገመ  እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሠላማዊት መንገሻ  ክልሉ አዲስ በመሆኑ ኮሮና የመከላከል ተግባር ከመደበኛ የጤና አገልግሎት ጋር አጣምሮ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጠው የቆዩ የዳዬን ጨምሮ የአራት ሆስፒታሎች የማስፋፊያ ስራዎች ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ጥበቡ አበበ በበኩላቸው ሆስፒታሉ መደበኛውን የጤና አገልግሎት ከኮሮና ቫይረስ ህክምና ጋር አጣምሮ ለማስኬድ የክፍሎች ጥበት ችግር እንዳለበት ተናግረዋል።

የመድኃኒት እጥረት በተለይ ተመላላሽ ታካሚዎች ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረገ በመሆኑ በተቻለ አቅም መፍትሄ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ሃኒባል አበራ እንዳሉት ደግሞ የከተማው ማህበረሰብ ከአመራሩ ጋር ባደረጉት ርብርብ ኮሮና በተፈራው ያህል አልተስፋፋም፡፡

የኮሮና መመርመሪያ ማሽን እጥረት በስራው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝና የኩላሊት እጥበት ስራው ላይ ጫና መፍጠሩን  ጠቁመዋል።

በጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ የተመራው ሉኡካን ከአካባቢው ነዋሪዎችና አመራሮች ጋር መወያየታቸውንም ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም