የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የፖለቲካ አቋሞች ላይ ስምምነት ተፈራረሙ

131

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የፖለቲካ አቋሞች ላይ ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ፓርቲዎቹ ለ10 ወራት ያህል በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ቆይተው በ10 ነጥቦች ላይ በመስማማታቸው የጋራ የፖለቲካ አቋሞቻቸው ላይ የስምምነት ፊርማ የተፈራረሙት።

የውይይታቸው መነሻ ባለፈው ዓመት በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግጭቶች መከሰታቸውና ከዚህ ጀርባ የፖለቲካ ተዋንያን አሉ በሚል ግንዛቤ ሁኔታውን ለማርገብ መሆኑ ተገልጿል።

የፓርቲዎቹን ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት ሕዳር ላይ ያስጀመሩ ሲሆን ፓርቲዎቹ በራሳቸው የመጀመሪያ ውይይታቸውን የጀመሩት በዛው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ነበር።

ውይይቱ ሲጀመር አምስት በአማራና አምስት በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የጀመሩት ሲሆን የብልጽግና ፓርቲም ተሳትፎ ነበረው።

ውይይቱን ከሁለቱም አካላት ገለልተኛ ሰዎች ተመርጠው ሲያወያዩ ቆይተው ውይይታቸው ውጤት በማምጣቱ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ውይይቶቹን ሲያስተባብሩ ከነበሩ ገለልተኛ አካላት መካከል ዶክተር ዲማ ነገዎ እና ዶክተር ገበያው ጥሩነህ ፓርቲዎቹ ከስምምነት ለመድረስ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የብልፅግና ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ውህደት፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የመላ አማራ ህዝብ ፓርቲ፣ ነፀብራቅ አማራ ድርጅት፣ የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት እና የአማራ ዴሞክራሲ ሃይል ንቅናቄ ናቸው።

ፓርቲዎቹ የደረሱባቸው ስምምነቶች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክርም ተገልጿል።

የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደረጉ ገለልተኛ አካላትን አመስግነዋል።

በፓርቲዎቹ ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

1. የአገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አካታች የሆነ ቀጣይ አገራዊ ውይይትና ድርድር ማካሄድ፤

2. ጥርጣሬ፣ መከፋፈል፣ እርስ በእርስ መቃረን፣ ወደ ዳር መገፋፋት፣ አንዱ የሌላውን ስም ከማጥፋት እንዲሁም ህዝብ ለህዝብ የሚያጋጩና ከሚያቃቅሩ ድርጊቶች መቆጠብ፤

3. አገራዊ የህዝብ ቆጠራ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ባለው አሰራር በማካሄድ የሁሉም የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች የህዝብ ብዛት በአግባቡ ተቆጥሮ እንዲታወቅ ማድረግ፤ የከዚህ በፊት ድክመቶችን የሚያርምና የማይደገም መሆኑን ማረጋገጥ።

4. በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መገንባት፣ የግልና የቡድን መብቶችን ማስከበርና በየጊዜውና በየደረጃው ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ፤

5. የኢትዮጵያን የታሪክ አቀራረብ የታሪክ አንጓዎችን ተከትሎ ከሁሉም ብሔርና ብሔረሰቦች በተውጣጡ የታሪክ ምሁራን የአገሪቱ ህዝቦች ግንኙነትና ታሪክ ጥናት እንዲካሄድ፤ የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም እንዲቋቋም፤

6. በኦሮሞና አማራ ክልሎች የሚኖሩ የሁሉም ህዝቦች አባላት ደህንነትና መብቶች እንዲከበር፤

7. በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታ፣ ህግና ፍትህን ማስፈን፤ ከየቦታው ያለ አግባብ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸውና ኑሮአቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፤

8. አገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግስት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዲሻሻል ማድረግ፤

9. በአገሪቱ ዘላቂና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ልማት ማጎልበት፤ የህዝቦቻችንን ፍትሃዊ የኢኮኖሚና የሃብት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤

10. የተለያዩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችንና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶችን በጋራ ማዘጋጀት የሚሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም