ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች በሞባይል ስልክ ቁጥራቸው ሊፈጸም ከሚችል ወንጀል እንዲጠነቀቁ አሳሰበ

304

መስከረም 13/2013(ኢዜአ) ሕገወጦች በደንበኞች በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት በመጠቀም የሚፈጸሙት የማጭበርበር ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቀ።

የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች የሞባይል ስልካቸው ሲጠፋ ወዲያው ባለማዘጋታቸው ወንጀለኞች ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች የሚጠቀሙበት መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ለኢዜአ በላከው መግለጫ በ2012 ዓ.ም ብቻ በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት በመፈጸሙ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ኪሣራ እንደዳረገው አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ደንበኞች የስልክ መስመራቸውን (ሲምካርዳቸውን) ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸውም  ለእንግልትና የወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት እየተዳረጉ መሆናቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

ደንበኞች በተለያየ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው ሲጠፋባቸው በ994 የጥሪ ማዕከል በመደወል፣ በ8994 በአጭር የጹሑፍ መልዕክት እና በይፋዊ የማኅበራዊ ድረገጾች በመጠቀም መሥመራቸውን እንዲያዘጉ ኢትዮ ቴሌኮም አሳስቧል።   

መግለጫው አያይዞም ደንበኞች በአቅራቢያቸው ከሚገኝ የሽያጭ ማዕከል ምትክ ሲም ካርድ እንዲወስዱና የስልክ መስመራቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው ባለመስጠት ከወንጀል ድርጊት ራሳቸውን እንዲከላከሉ አሳስቧል።

ኢትዮ ቴሌኮም በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋቱ ቀደም ሲል የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም ሲፈጸሙ የነበሩ የማጭበርበር ወንጀሎች መቀነሱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም