በቡራዩ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጥንቃቄ የታከለበት የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል

94

አዲስ አበባ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) በቡራዩ ከተማ የኮሮናቫይረስን የመከላከል ጥንቃቄ በማድረግ የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው። 

በትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውንም የከተማዋ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ለወላጆች፣ ለተማሪዎችና ለማኅበረሰቡ ስለወረርሽኙ መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ንጋቱ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶችም የመማሪያ ክፍሎች ማስፋፋት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የመጸዳጃ ቤቶች እድሳትና አዲስ የመገንባት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ተማሪዎች ጥንቃቄ በማድረግ ያለስጋት ምዝገባ እያካሄዱ ነው፤ ትምህርት ሲጀመርም ተማሪዎች በፈረቃ የሚማሩ ይሆናል ብለዋል።

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግና እጆቻቸውን በመታጠብ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ተፈሪ ገለጻ ለመምህራንም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ሳኒታይዘርና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ይቀርብላቸዋል።


በከተማዋ ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምዝገባ መጀመሩንና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እየተገነቡላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪ ክፍሎች የማስፋፊያ ስራው ተቋማትና ኅብረተሰቡ እየተሳተፉ ሲሆን የአኳ አዲስ ውሃ ፋብሪካ 220 የጣራ ቆርቆሮ ለቡራዩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ በድጋፍ አበርክቷል።

የድርጅቱ የውጭ ጉዳይና የሠራተኞች ኃላፊ አቶ ተክሉ ከተማ ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት ድጋፉን አድርጓል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ የዛሬውን ሳይጨምር በከተማዋ ድጋፍ ለሚያሻቸው ሰዎች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ማበርከቱንም አስታውሰዋል።

ድርጀቱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

የተማሪዎችን መጨናነቅ በመቀነስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በትምህርት ቤቶች ከ32 ሺህ በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም