በትግራይ የግእዝ ቋንቋ በመደበኛ ትምህርት መርሀግብር ሊሰጥ ነው

244

መቐለ፣ መስከረም 13 /2013 ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል የግእዝ ቋንቋን በመደበኛ የትምህርት መርሀ ግብር ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ቋንቋዎች አካዳሚና ትምህርት ቢሮ አስታወቁ።

የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ተክሉ ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገሪቱ በግእዝ ቋንቋ የታተሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ የብራናና የመጽሀፍት ህትመቶች አሉ።

"አዲሱ ትውልድ ፅሁፎችን በማንበብ የሀገሩን ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ታሪክና ማንነት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ለማበረታታት የቋንቋውን ትምህርት መስጠት አስፈልጓል" ብለዋል።

በተያዘው 2013 አመት በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምሀርቱን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል ።

ከትግርኛ፣ ኩናምኛና ሳሆኛ ቋንቋዎች ቀጥሎ ግዕዝ አራተኛ ቋንቋ ሆኖ በክልሉ በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

ቢሮው የመማር ማስተማር ስራውን እንዲጀምር በክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ መጽደቁንም አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን በክልሉ በሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስጀመር የመምህራንና የመማሪያ መፃፍት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ከስድስት ወራት በኋላ ትምሀርቱን ለመጀመር እቅድ መያዙን አመላክተዋል ።

በመቐሌ የሃወልት ክፍለ ከተማ ነዋሪና የሰላም አካዳሚ የትግርኛ ቋንቋ መምህር ሃዱሽ አታክልቲ የግዕዝ ቋንቋ በመደበኛ የትምህርት መርህ ግብር እንዲሰጥ መታቀዱ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርቱ መሰጠት በየአብያተ ክርስትያናትና ገዳማት ውስጥ የሚገኙና በግዕዝ ቋንቋ ተጽፈው የታተሙ ጥንታዊና ታሪካዊ መፃህፍቶችን በቀላሉ አንብቦ ለመገንዘብ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል ።

ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት እድገትም ያለው አስተዋጽኦ  የጎላ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

"አዲሱ ትውልድ በመጤ ቋንቋዎችና ባህሎች ከመበረዝ ይልቅ የሀገሩን ባህልና ቋንቋ በሚገባ እንዲያውቅና እንዲጠብቅ ያስችለዋል" ሲሉም መምህር ሃዱሽ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም